መምህራኑ ወርሃዊ ደመዛቸው ከ24 ሺህ ፓውንድ ወደ 69 ሺህ እንዲያድግ ጠይቀዋል
የሱዳን መምህራን ደመወዝ ይጨመርልን በሚል የአንድ ቀን አድማ መትተዋል።
በሱዳን በዛሬው ዕለት መምህራን በሀገር አቀፍ ደረጃ አመጽ ላይ ሲሆኑ አድማውን ተከትሎም ከ20 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ተገልጿል፡፡
መምህራኑ ለአንድ ቀን የሚቆይ አመጽ ያካሄዱት እየተከፈላቸው ያለው ወርሃዊ ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ መንግስት የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርግላቸው በማሰብ ነው፡፡
የ"ክብር አመጽ" የሚል መጠሪያ የተሰጠው የአሁኑ የሱዳን መምህራን አመጽ እየተከፈላቸው ባለው ደመወዝ መኖር እንዳልቻሉ፣ የኑሮ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የሱዳን መምህራን ባሳለፈው መጋቢት ላይ ተመሳሳይ አመጽ አድርገው የነበረ ቢሆንም መንግስት ለጥያቄያቸው ምላሽ ሊሰጥ እንዳልቻለም አክለዋል፡፡
በሱዳን የአንድ መምህር መነሻ ወርሃዊ ደመወዝ 24 ሺህ የሱዳን ፓውንድ ሲሆን ይህ የመነሻ ደመወዝ ወደ 69 ሺህ ፓውንድ እንዲያድግ መምህራኑ ጠይቀዋል፡፡
የሱዳን መንግስት ይሄንን ለመምህራን ካላደረገ በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመረ ላለው የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ መናር ምክንያት ስራቸውን በሚገባ መስራት እንደማይችሉ የሀገሪቱ መምህራን ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
ይሁንና መንግስት ከመምህራን የተነሳውን ጥያቄ ምላሽ ካሰጠ በህገ መንግስቱ መሰረት ጥያቄያቸውን እንደሚቀጥሉበት ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
በሱዳን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ያሉ መምህራን የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ሲሆን የአንድ መምህር ወርሃዊ ደመወዝ ከ50 ዶላር በታች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የትምህርት ዘርፍ በሱዳን የመንግስትን ትኩረት ባለማግኘቱ ተገቢ በጀት እየተበጀተለት አይደለም የሚሉት መምህራኑ በሱዳን የትምህርት ታሪክ አሁን ላይ የተጎዳ መስክ ሆኗልም ብለዋል፡፡