ስዊዝ ባንክ ገንዘብን በአስተማማኝ መልኩ ለማስቀመጥ የሚመረጥ ስመጥር ባንክ መሆኑ ይነገራል
የስዊዝ ብሄራዊ ባንክ (ስዊዝ ባንክ) በፈረንጆቹ 2023 ዓመት የ3 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠመው አስታወቀ።
ከስዊዝ ባንክ የወርቅ ይዞታ የተገኘው የዋጋ ጭማሪ እንዲሁም አደጋ ወቅት በተሰጡት የአደጋ ጊዜ ብድሮች ላይ የተከፈለው ወለድ የዋጋ ግሽበትን ለመቅረፍ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የሚከተልበትን ማዕከላዊ ባንክ ወጪ ማካካስ አልቻለም።
ኪሳራው በአብዛኛው ያጋጠመው በዋናነት ለንግድ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚከፈለው ወለድ ላይ ባደረገው ጭማሪ ምክንያት መሆኑንም ሮይትስ ዘግቧል።
የባንኩ የጥር ወር ጊዜያዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ ባንኩ አሁን ላይ ያስመዘገበው ውጤት በፈረንጆቹ 2022 ካጋጠመው ታሪካዊ ኪሳራ እያገገመ መምጣን ያመለክታል ተብሏል።
ስዊዝ ባንክ በፈረንጆቹ 2022 ላይ በታሪኩ ከባድ የሚባል ኪሳራ እንዳጋጠመው ይታወሳል።
በወቅቱም የስዊዝ ብሄራዊ ባክ እንዳስታወቀው በፈረንጆቹ 2022 የበጀት አመት 132 ቢሊዮን የስዊዝ ፍራንክ ወይም 143 ቢሊዮን ዶላር ከስሯል።
ይህ ኪሳራ ባንኩ በ116 ዓመት ታሪኩ ትልቁ እና መጠኑም የስዊዘርላንድን 18 በመቶ የሀገር ውስጥ ገቢ ወይም ጂዲፒ ጋር የሚመጣጠን እንደሆነም በወቅቱ መነገሩ ይታወሳል።
ባንኩ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበው ኪሳራ በፈረንጆቹ በ2015፤ 23 ቢሊዮን ፍራንክ ነበር። በዚህም ምክንያት ባንኩ የተለመደውን ክፍያ ለስዊዘርላንድ መንግስት ሳይፈጽም ቀርቷል፤ ለባለ አክሲዮኖቹም የሚከፈለው ክፍያ ተጎድቷል።
ባንኩ በፈረንጆቹ 2021፣ 26 ቢሊዮን ፋራክ ትርፍ እንዳገኘ ሪፖርት አድርጎ ነበር።
ስዊዝ ባንክ ገንዘብን በአስተማማኝ መልኩ ለማስቀመጥ የሚመረጥ ስመጥር ባንክ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል።