400 ሜትር ርዝመት ያለው መርከብ በከፍተኛ ንፋስ ምክንያት በጎኑ ተዘርግቶ በመቆም ነው ቦዩን የዘጋው
በዓለም ላይ እጅግ ከተጨናነቁ የንግድ መርከብ መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው የግብፁ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ፣ ከትናንት ጀምሮ በአንድ ግዙፍ የጭነት መርከብ ተዘግቷል፡፡
ቦዩ እንዲዘጋ ያደረገው የታይዋን ኤቨርግሪን የባህር ትራንስፖርት ኩባንያ ንብረት የሆነው የ224 ሺ ቶን ክብደት ፣ 400 ሜትር ርዝመት እና 59 ሜትር ስፋት ያለው ‘ኤቨር ጊቭን’ የተሰኘ መርከብ ነው፡፡ መርከቡ በከፍተኛ ንፋስ በድንገት በመመታት በቦዩ መተላለፊያ ላይ በጎኑ ተዘርግቶ በመቆም ነው ቦዩ እንዲዘጋ ያደረገው ተብሏል፡፡
መርከቡ ትናንት ማክሰኞ ጠዋት ከቀይ ባህር ወደ ሜዲተራኒያን ባህር በሚሻገርበት ወቅት አደጋው ማጋጠሙን ኤቨርግሪን ኩባንያ አስታውቋል፡፡ በወቅቱ ከኋላው የነበሩ ሌሎች 15 መርከቦች መስተጓጎል ገጥሟቸዋል፡፡
ይሁንና የስዊዝን ቦይ የዘጋው መርከብ፣ በቆመበት ለቀናት ሊቆይ ይችላል በሚል ስጋት ግብፅ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የቀድሞውን የቦዩን ሰርጥ መክፈቷን አስታውቃለች፡፡ መርከቡን ከስፍራው ለማንሳት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ እና በተወሰነ ደረጃ መርከቡን ማንቀሳቀስ እንደተቻለም ነው ሀገሪቱ የገለጸችው፡፡
ስዊዝ ቦይ የዓለማችን 10 በመቶ የሚሆነው የንግድ መርከብ የሚመላለስበት ፣ ሜዲተራኒያን ባህርን ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኝ መተላለፊያ መስመር ነው፡፡ ይህ ቦይ እሲያ እና አውሮፓ በአቋራጭ የሚገናኙበት መስመርም ነው፡፡