የሶሪያ ጊዜያዊ መሪ በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አራት አመት ይወስዳል አሉ
ምርጫ ለማካሄድ የሶሪያ የፖለቲካ ሃይሎች ብሄራዊ ምክክር አድርገው ህገመንግስቱን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አህመድ አል ሻራ ተናግረዋል
እስራኤል በበኩሏ በሶሪያ የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ድብደባዋን ቀጥላለች
የሶሪያ ጊዜያዊ መሪ አህመድ አል ሻራ በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አራት አመት ይወስዳል አሉ።
አል ሻራ ከሳኡዲው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ "አሁን ያገኘነው እድል በአምስት ወይም በ10 አመት አይገኝም፤ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህገመንግስት ያስፈልገናል" ብለዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች ብሄራዊ ምክክር አድርገው ህገመንግስቱን ለማሻሻል ጊዜ እንደሚወስድ በመጥቀስም ምርጫ ለማካሄድ በጥቂቱ አራት አመት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የበሽር አል አሳድ አገዛዝን ለመጣል የተካሄደውን ፈጣን እንቅስቃሴ የመራው ሃያት ታህሪር አል ሻም ፈርሶ ታጣቂዎች ወደ ሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግም ነው ያነሱት።
ሶሪያ የፍትህ ስርአቷን ብሎም የመንግስት ተቋማቷን ዳግም ወደ ስራ ለማስገባትና የህዝብ ቆጠራ ለማድረግም ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋታል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሶሪያ ከ53 አመታት የአሳድ አገዛዝ ነጻ ብትወጣም የወደፊት እጣ ፈንታዋ አሁንም ድረስ አልታወቀም።
እስከ መጋቢት 1 2025 በስልጣን ላይ ይቆያሉ የተባሉት አህመድ አል ሻራም ስልጣናቸውን በማራዘም በ13 አመታት የእርስ በርስ ጦርነት የተተከፋፈለችውን ሀገር ወደ አንድ የማምጣት ቃላቸውን ላይጠብቁ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
የተለያየ ፍላጎት ያላቸውና የውጭ ሀገራት ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የፖለቲካ ሃይሎችን የማቀራረቡ ጥረትም ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በሌላ በኩል የሶሪያን ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች አወድማለሁ ስትል የዛተችው እስራኤል የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።
በትናንትናው እለትም በደማስቆ አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተቀማጭነቱን ብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ገልጿል።
የእስራኤል ጦር ግን አብዛኞቹ ንጹሃን ሞተውበታል ስለተባለው ጥቃት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ኢራንን ደጋግመው የወቀሱት አህመድ አል ሻራ ከሌላኛዋ የአሳድ አጋር ሩሲያ ጋር "ስትራቴጂካዊ ትብብር" ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ እየተዘገበ ነው።
የሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን መሪው በሰሜን ምስራቃዊ ሶሪያ ከሚንቀሳቀሱት የሶሪያ ዴሞክራቲክ ሃይሎች (ኤስዲኤፍ) ጋር ድርድር መጀመሩንና የታጠቁት ሃይሎች የሶሪያን የደህንነት ተቋማት እንደሚቀላቀሉ ተስፋ ማድረጋቸውን ለአል አረቢያ ተናግረዋል።
ቱርክ የምትደግፋቸው የሶሪያ ታጣቂዎች ከኤስዲኤፍ ሃይሎች ጋር እየተዋጉ ነው፤ ማንቢጅ የተባለችውን ከተማ መቆጣጠራቸውም ሶሪያ ከአሳድ መውደቅ በኋላም ፈተናዋ የበዛ መሆኑን አመላክቷል።