በሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልኡክ ሳኡዲ ገባ
ከ11 ቀናት በፊት የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳድ አል ሺባኒ በደማስቆ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ እየጠየቁ ነው
ሶሪያ ባለፈው አመት ዳግም ወደ አረብ ሊግ የተመለሰችው በሳኡዲ ድጋፍ ነበር
በሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል ሺባኒ የተመራ ልኡክ በሳኡዲ ይፋዊ ጉብኝት እያደረገ ነው።
ሺባኒ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሙርሃፍ አቡ ቃስራ እና ከደህንነት ሃላፊው አናስ ካታብ ጋር ሪያድ መግባታቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
"በነጻዋ ሶሪያ ታሪክ የመጀመሪያ ጉብኝታችን ነው፤ በሶሪያ እና ሳኡዲ ታሪካዊ ግንኙነት ውስጥ አዲስና ብሩህ ገጽ መክፈት እንፈልጋለን" ሲሉም አክለዋል።
የሶሪያ ብሄራዊ የዜና ወኪል ልኡካኑ ወደ ሪያድ ያቀናው በሳኡዲ መንግስት ግብዣ መሆኑን ዘግቧል።
የበሽር አል አሳድን አገዛዝ አስወግዶ ስልጣን በያዘው ሃይል ከ11 ቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የተሾሙት ሺባኒ በሳኡዲ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ነው እያደረጉ የሚገኙት።
ልኡክ እየመሩ ወደ ሪያድ ማቅናታቸውም ደማስቆ ከሪያድ ጋር ትብብሯን ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ያመላክታል ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
የሳኡዲ ልኡካንም ባለፈው ወር በደማስቆ ከሶሪያ ጊዜያዊ መሪ አህመድ አል ሻራ ጋር መምከራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሳኡዲ መንግስት ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
አል ሻራ ባለፈው ሳምንት ከሳኡዲው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሳኡዲ አረቢያ "በሶሪያ መጻኢ ትልቅ ድርሻ ይኖራታል" ማለታቸው ይታወሳል።
በ13 አመታቱ የእርስ በርስ ጦርነት የፈራረሰውን የሶሪያ መሰረተ ልማት ማደስ ከተቻለ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እድል እንዳለም ነው ያነሱት።
ሶሪያ ባለፈው አመት ዳግም ወደ አረብ ሊግ እንድትመለስ የሳኡዲ አረቢያ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል።
አዲሱ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል ሺባኒ እና የመሩት ልኡክ በሳኡዲ ቆይታው የሪያድ እና ደማስቆን ትብብር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል።
አል ሺባኒ ምዕራባውያን በአሳድ አገዛዝ ወቅት በሶሪያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጀምረዋል።
አሳድ በ2011 ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን እርምጃዎችን መውሰድ ሲጀምሩ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ስዊዘርላንድ ማዕቀቦችን መጣላቸው ይታወሳል።