አዲሱ የሶሪያ መሪና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደማስቆ ውስጥ ተነጋገሩ
ኪቭ የበሽር አላሳድ አስተዳደርን ካስወገደው ቡድን ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ጥረት እያደረገች ነው ተብሏል

ዘለንስኪ ሀገራቸው የሩሲያ አጋር ተደርጋ ስትታይ ለነበረችው ሶሪያ የመጨረሻውን ዙር እርዳታ መላኳን ገልጸዋል
አዲሱ የሶሪያ መሪና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደማስቆ ውስጥ ተነጋገሩ።
በይፋ ያልተሾመው አዲሱ የሶሪያ መሪ አህመድ አል ሻራ በዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲይቢሃ የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ተቀብሎ ማነጋገሩን ሮይተርስ የሶሪያ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኪቭ የበሽር አላሳድ አስተዳደርን ካስወገደው ቡድን ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ጥረት እያደረገች ነው ተብሏል።
ስለንግግራቸው ዝርዝር ጉዳይ በሶሪያ በኩል የተገለጸ ነገር ለየም። የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው የሩሲያ አጋር ተደርጋ ስትታይ ለነበረችው ሶሪያ የመጨረሻውን ዙር እርዳታ ባለፈው አርብ እለት መላኳን ገልጸዋል።
ዘለንስኪ 'ግሬን ፍሮም ዩክሬን' በሚለው የኪቭ ሰብአዊ መርሃግብር አማካኝነት 500 ሜትሪክ ቶን የስንዴ ዱቄት ወደ ሶሪያ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል። አለምአቀፍ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች አምራች የሆነችው ዩክሬን የፕሬዝደንት በሽር አላሳድን ከስልጣን መውደቅ እና ወደ ሩሲያ መኮብለል ተከትሎ ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሻሻል ትፈልጋለች።
በአሁኑ ወቅት 'ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ' ከከፈተችባት ሩሲያ ጋር እየተፋለመች ያለችው ዩክሬን ከዚህ በፊት ስንዴ እና በቆሎ ለመካከለኛው ምስራቅ ስታቀርብ የቆየች ቢሆንም ለሶሪያ ግን አታቀርብም ነበር።
ሩሲያ ለሶሪያ የምታቀርበው ስንዴ አሁን በሶሪያ ባለው አለመረጋጋት እና በክፍያ መዘግየት ምክንያት ማቆሟን ሮይተርስ ዘግቧል። ሩሲያ ምዕራባውያን በሞስኮ እና ደማስቆ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለማለፍ ውስብስብ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክ አማራጮችን በመጨቀም ለሶሪያ ስንዴ ስታቀርብ ቆይታለች።
የአሳድ አገዛዝን ያስወገደው ሀያት ታህሪር አልሻም የተባለው እስላማዊ ቡድን ሶሪያ ውስጥ የሚገኙትን የሩሲያ የጦር ሰፈሮች የወደፊት እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል ተብሏል። የሩሲያ የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በሶሪያ ያሉት የሩሲያ ጦር ሰፈሮች በደማስቆ ካለው አዲስ አስተዳደር ጋር የመወያያ ጉዳይ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
አል ሻራ ከሩሲያ ጋር የሚኖር ግንኙነት የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ወር ተናግሯል።