አዲሱ የሶሪያ አስተዳደር ለመንግስት ሰራተኞች 400 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ሊያደርግ ነው
1.65 ትሪሊየን የሶሪያ ፓውንድ ያስወጣል የተባለው የደመወዝ ጭማሪ በተለያዩ ሀገራት እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ የሀገሪቱን ንብረቶች በማስለቀቅ ተግባራዊ ይደረጋል ነው የተባለው
አዲሱ አስተዳደር ለ13 አመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት የወደቀውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እሰራለሁ ብሏል
የመንግስት ስራ ቅልጥፍናን እና ተጠቂነትን ለማሳደግ ለመንግስት ሰራተኞች 400 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ አዲሱ የሶሪያ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር እንዳሉት የሚኒስትሮች አስተዳደራዊ መዋቅር ከተጠናቀቀ በኋላ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪው ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
ጭማሪው 1.65 ትሪሊዮን የሶሪያ ፓውንድ ወይም አሁን ባለው የምንዛሪ ምጣኔ ወደ 127 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ ይገመታል፡፡
አስተዳደሩ በነባር የመንግስት ሀብቶች ፣ በቀጠናዊ አጋሮች ዕርዳታ፣ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እና በውጪ የሚገኙ የሶሪያ ንብረቶችን በማስለቀቅ የጭማሪውን ወጪ ለመሸፈን ወጥኗል፡፡
የፋይናንስ ሚኒስትሩ መሀመድ አባዚድ በሀገሪቱ ለሚገኝው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ማሻሻያው ለ13 ዓመታት በዘለቀው ግጭት እና ማዕቀብ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት አዲሱ የሶሪያ ጊዜያዊ መንግስት የዘረጋው ሰፊ ስትራቴጂ አካል ነው ተብሏል፡፡
በተገረሰሰው የፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ መንግስት ስር የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በወር 25 ዶላር የሚጠጋ ሲሆን ይህም አብዛኛው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዲኖር እንዳደረገው የገንዘብ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡
የደመወዝ ጭማሪው በመንግስት ሰራተኝነት የተመዘገቡ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞችን በቂ እውቀት ፣ የትምህርት ዝግጅት እና በሀገሪቱ መልሶ ግንባታ ላይ አስፈላጊ ክህሎት ያላቸውን እንዲሁም ሀሰተኛ ደመወዝ ተከፋዮችን በመለየት አጠቃላይ ግምገማን ተከትሎ የሚደረግ ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሶሪያ መንግስት ግምጃ ቤት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት አለበት፤ በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ያለው አብዛኛው ገንዘብ የሶሪያ ገንዘብ ሲሆን እሱም ቢሆን በጦርነቱ ምክንያት የመገበያያ አቅሙን አጥቷል፡፡
ሆኖም አዲሱ መንግስት ከቀጠናዊ አጋሮች እና ከአረብ ሀገራት የውጭ ሀገራት ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለት ቃል ተገብቶለታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የውጭ ሀገራት እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው የቆዩ የሶሪያ መንግስት ንብረቶችን በማስመለስ እስከ 400 ሚሊየን ዶላር ድረስ ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡