ዩክሬን ከአሜሪካ ያልመጣ የደህንነት ዋስትና እንደማትቀበል ዘለንስኪ ተናገሩ
ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ኪቭ ጦርነቱን ለማቆም የምትስማማው አሜሪካ የደህንነት ዋስትና ከሰጠቻት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል
ዘለንስኪ ዋሸንግተን ከኔቶ የምትወጣ ከሆነ ሩሲያ ወደ አውሮፓ ማጥቃቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል
ዩክሬን ከአሜሪካ ያልመጣ የደህንነት ዋስትና እንደማትቀበል ዘለንስኪ ተናገሩ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ኪቭ ጦርነቱን ለማቆም የምትማማው አሜሪካ የደህንነት ዋስትና ከሰጠቻት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ተመራጩ ፕሬዝደንት ትራምፕን ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ እንደሚያገኛቸው ተስፋ አድርገዋል።
ዘለንስኪ ከአሜሪካው ፖድካስተር ፍሪድማን ጋር ባደረጉት እሁድ እለት በተላለፈው ቃለ ምልልስ ዩክሬናውያን ትራምፕ ሞስኮ እያካሃደች ያለውን ጦርነት እንድታቆም ያደርጓታል ብለው እንደሚተማመኑ እና ዋሸንግተን ከሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጥምረት የምትወጣ ከሆነ ሩሲያ ወደ አውሮፓ ማጥቃቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ የትራምፕ መመለስ ጦርነቱን ለማስቆም ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም ፈጣን ሰላም ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ኪቭ ስጋት ገብቷታል።
ዘለንስኪ ለሶስት ሰአታት በቆየው ቃለ ምልልስ ዩክሬን የደህንነት ዋስትና ሳይኖራት ጦርነቱን ማቆም ሩሲያ ድጋሚ ታጥቃ ጥቃት እንድትፈጽም መፍቀድ ነው ብለዋል።
የዩክሬኑ መሪ በትራምፕ የሚመራው አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና በመስጠት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው፣ እሳቸው እና ትራምፕ "በጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ሰላም" አስፈላጊነት ላይ መግባባታቸውን ገልጸዋል።
"ያለ አሜሪካ እና የደህንነት ዋስትና የማይቻል ነው፣ ለማለት የፈለኩት የሩሲያን ጥቃት ስለሚያስቆሙ የደህንነት ዋስትናዎች ነው" ሲሉ ዘለንስኪ የአውሮፓ ደህንነት የራሱንም ለመቆጣጠር የማይችል ደካማ መሆኑን አመላክተዋል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ለእውነተኛ ንግግር ዝግጁ አለመሆናቸውን የገለጹት ዘለንስኪ የክሬሚሊን መሪዎች ለዘላቂ ሰላም እንዲስማሙ መገደድ አለባቸው ብለዋል።
በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ ጦርነቱ ከተጀመረበት 2022 የመጀመሪያ ወራት ወዲህ ለዩክሬን ፈታኝ ሲሆን በሩሲያ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ወታደሮች በምስራቅ ዶምባስ ግዛት በተከታታይ መንደሮችን እየለቀቁ ይገኛሉ።
የመወሰን ጉዳይ የአሜሪካ ነው ያሉት ዘለንስኪ በትራምፕ አስተዳደር ስር የምትሆነው አሜሪካ ኔቶን ለቃ ለመውጣት ከወሰነች ኔቶ እንደሚዳከም እና ፑቲን የልብ ልብ እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ አስጠንቅቀዋል።
"ይህ ማለት አሜሪካ ለቃ የምትወጣ ከሆነ ፑቲን አውሮፓን ያወድማታል" ብለዋል ዘለንስኪ።
የዩክሬኑ መሪ ክሬሚሊንን በማስቆም ጉዳይ ከትራምፕ ጋር ቁጭ ብለው መነጋገር እንደሚያስፈልጋቸው እና የአውሮፓ ሀገራትም ዩክሬን ለንግግር ከመቀመጧ በፊት ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ብለዋል።