የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት የውጭ ጉዞ ኳታርን ጎበኙ
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኳታር ጉብኝት ፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት የውጭ ሀገር ጉብኝት ነው
አልሽባኒ የመጀመሪያቸውን የውጭ ሀገር ጉብኝት ያደረጉት በሳኡዲ አረቢያ ነበር
የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት የውጭ ጉዞ ኳታርን ጎበኙ።
በአዲሶቹ የሶሪያ መሪዎች የተመረጡት የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሀሰን አል ሽባኒ የኳታሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸክ መሀመድ ቢን አብዱል ራህማን አልታኒን ለማግኘት በዛሬው እለት ዶሃ መድረሳቸውን ሮይተርስ የኳታር ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሶሪያ ልኡክ ቡድን የሀገሪቱን መከላከያ ሚኒስትር ሙርሃፍ አቡ ቋስራንና የደህንነት ኃላፊውን አናስ ካታብን ማካተቱን የሶሪያ ዜና አገልግሎትን ማረጋገጡን ዘገባው ጠቅሷል።
የልኡክ ቡድኑ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጭምር የሚያገለግሉትን ሸክ መሀመድን እና ሌሎች ከፍተኛ የኳታር ባለስልጣናትን ያገኛል ተብሏል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኳታር ጉብኝት ሶሪያን ለ 24 አመታት ያስተዳደረው ፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት የውጭ ሀገር ጉብኝት ነው።
አለሸባኒ የሶሪያን "መረጋጋት፣ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ማገገም እና ልዩ ግንኘነት ለመገንባት" በዚህ ሳምንት አረብ ኢሜሬትስን እና ጆርዳንን እንደሚጎበኙ በኤክስ ገጻቸው ገልጸዋል። አልሽባኒ የመጀመሪያቸውን የውጭ ሀገር ጉብኝት ያደረጉት በሳኡዲ አረቢያ ባለፈው ረብዕ እለት ነበር። ሚኒስትሩ በሳኡዲ ጉብኝታቸው የሶሪያ ሽግግር እንዴት መመራት አለበት በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ከሳኡዲ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የበሽር አልአሳድ አስተዳደርን በማስወገድ ቀደሚ ሚና የነበረው አማጺ ቡድን ሀያት ታህሪር አልሻም ቡድን መሪ አህመድ አልሻራ በይፋ ባይመረጥም ጊዜያዊ የሶሪያ አስተዳደርን እየመራ ነው።