አሳድ በሶሪያ እና በአካባቢው ያለው ሁኔታ አጠቃላይ እልባት ስለሚያገኝበት ሁኔታ ከፑቲን ጋር ይመክራሉ ተብሏል
የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሞስኮ ገቡ፡፡
ከሚስትሮቻቸው ጋር ወደ ሞስኮ ያቀኑት አሳድ በጉብኝታቸው ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአንኳር ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የሶሪያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በቴለግራም ገጹ ላይ ባወጣው መገለጫ አስታውቋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በፖለቲካ፣ ንግድ እና ሰብአዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመተባበር እንዲሁም "በሶሪያ እና በአካባቢው ያለው ሁኔታ አጠቃላይ እልባት ስለሚያገኙበት ሁኔታ" እንደሚወያዩም ተጠቅሷል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ካለፈው ወር አስከፊ ርዕደ መሬት በኋላ ከመካከለኛው ምስራቅ ውጭ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉብኝት ነው፡፡
- ሩሲያ በደረሰው “ጠንካራ” የመሬት መንቀጥቀጥ ሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋሞቼ ጉዳት አልደረሰባቸውም አለች
- የቱርኩ ፕሬዝደንት ስለሰላም ለመምከር ከሶሪያው በሽር አል አሳድ ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉ ተናገሩ
የሶሪያን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ሞስኮ እንደፈረንጆቹ በ2015 የአሳድን መንግስት በመደገፍ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዷ አይዘነጋም፡፡
ሩሲያ የአየር ላይ ቦምብ በመወርወር ያካሄደችው ስኬታማ ወታደራዊ ዘመቻ የሶሪያ አማጺዎች ከቁልፍ ወታዳራዊ ይዞታዎች ለቀው እንዲወጡ ያስገደደ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ዘመቻው ፕሬዝዳንት አሳድ በአማጽያን ስር የነበሩ በርካታ ግዛቶች መልሰው እንዲቆጣጠሩ ያስቻለም ነበር፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሞስኮ በሶሪያ ላታኪያ ግዛት በሚገኘው ሃሜሚም ስፍራ ቋሚ የአየር ማረፊያ እስከ ማቋቋም ደርሳለች፡፡
በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው ታርቱስ የሚገኘው የሩሲያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ውጭ ያለው የሩሲያ የባህር ኃይል ብቸኛው ቋሚ ወደብ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የፕሬዝዳንት አሳድ ጉብኝት 12 አመታት ካስቆጠረውና በሰላማዊ ሰልፍ የጀመረው የመጋቢት 2011ዱ የሶሪያ ህዝባዊ አመጽ ያገናኙትም አሉ፡፡
የሶሪያ የተቃዋሚዎች ጥያቄ ወደ አመጽ ተሸጋግሮ ሀገሪቱን አሁን ወዳለችበት ቀውስ የከተተው ፤ፕሬዝዳንት አሳድ ህዝብን ጥያቄ በኃይል ለመጨፍለቅ የወሰዱትን የተሳሳተ እርምጃ ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በአስከፊ ግጭቶች የታጀበው የሶሪያ ቀውስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁን የሰው ልጆች የመፈናቀል ችግር ያስከተለም ሆኗል፡፡