ሩሲያ በደረሰው “ጠንካራ” የመሬት መንቀጥቀጥ ሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋሞቼ ጉዳት አልደረሰባቸውም አለች
በሶሪያ በተከሰተው ርዕደ መሬት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 237 ደርሷል
የሩሲያ የጦር ኃይሎች አባላት ሙሉ በሙሉ ስራቸውን እያከናወኑ ነውም ተብሏል
የሩስያ መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በሶሪያ ያለውን አገልግሎት በሙሉ በመደበኛነት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ሰኞ ዕለት በመካከለኛው ቱርክ እና በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ላይ “ጠንካራ” የተባለ ርዕደ መሬት ተከስቷል።
አደጋውን ተከትሎ በሶሪያ በሚንቀሳቀሱት የሩሲያ ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን ሚንስቴሩ ጠቁሟል።
የሩሲያ መከላከያ "የሩሲያ ኃይሎች በመደበኛነት እየሰሩ ናቸው" በማለት አጽንኦት ሰጥቷል።
"የሩሲያ የጦር ኃይሎች አባላት ሙሉ በሙሉ ስራቸውን እያከናወኑ ነው። እና በሩሲያ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ምንም ዓይነት ጥፋት ወይም ጉዳት የለም" ብሏል።
"አውዳሚ" የተባለ ርዕደ መሬት ዛሬ ረፋድ ላይ በቱርክ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 የተመዘገበ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ደርሷል።
በበርካታ የአረብ ሀገራት በተለይም በሊባኖስ፣ በግብጽ፣ በኢራቅ እና በሶሪያ ከፍተኛ ርዕደ መሬት ደርሷል።
የሶሪያ የቴሌቭዥን ጣቢያ አል-ኢክበርያ በሶሪያ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 237 መድረሱን እና ቢያንስ 639 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።