የታይዋን ፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ ዌን ቻይናን አስጠነቀቁ
የታይዋን ጉዳይ ኃያላኑ አሜሪካን እና ቻይና ፍጥጫ ውስጥ የከተተ ዓለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል
ፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ ዌን “ታይዋን የቻይና አካል የመሆን ፍላጎት የላትም” ብለዋል
የታይዋን ፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ ዌን “በነጻነት እና ዴሞክራሲ አንደራደርም” ሲሉ ቻይናን አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቷ የሀገሪቱ ብሄራዊ ቀንን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር ደሴቲቱ የዩክሬን እጣፈንታ እንዳይገጥማት ብላ ዴሞክራሲያዊ አኗኗሯን የምትተውበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
የታይዋን 23 ሚሊዮን ህዝብ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የማያቋርጥ የወረራ ስጋት ውስጥ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡
ቻይናም ብትሆን እንደ ግዛቷ የምትያት ታይዋንን ከመጠቅለል የሚያግዳት ነገር እንደሌለ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ወታደራዊ አማራጭ ሁሉ ልትትጠቀም እንደምትችል በተለያዩ ወቅቶች ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
የታይዋንዋ ፕሬዝዳንት ግን የቤጂንግ ፍላጎት ዴሞክራሲና ነጻነትን ማጣጣም ከጀመሩ ታይዋናውያን ጋር ፍጹም የማይሄድ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
"እነዚህ ወታደራዊ መስፋፋቶች ለነጻ እና ዲሞክራሲያዊ የዓለም ስርአት የሚያመጡትን ፈተና በፍጹም ችላ ማለት አንችልም።እነዚህ እድገቶች (ዴሞክራሲና ነጻነት) ከታይዋን ጋር የማይነጣጠሉ ናቸው"ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፡፡
ታይዋን የቻይና አካል የመሆን ፍላጎት የላትም ያሉት ፕሬዝዳንቷ"በታይዋን ህዝብ እና በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን መካከል ያለው ሰፊ መግባባት ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን፣ ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ አኗኗራችንን መጠበቅ እንዳለብን የሚያሳይ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
"በዚህ ጉዳይ ላይ ለመደራደር ምንም ቦታ የለንም " ማለታቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የታይዋን ፕሬዝደንት ጻይ ኢንግ ዌን በቅርቡ በበሰጡት መግለጫ ሀገራቸው ማንንም እንደማትተነኩስና እና ነገርግን ራሷን እንደምትከላከል መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የቻይና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለታይዋን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነም ገልጸው ነበር፡፡
“የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ለመጠበቅ እራሳችንን እንሰጣለን” ያሉት ፕሬዝዳንቷ ዐጫለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍትሃዊ ያልሆኑ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም እንዲተባበርም ጠይቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የታይዋን ጉዳይ ሁለቱም ኃያላን ሀገራት አሜሪካና ቻይናም ፍጥጫ ውስጥ የከተተ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ “የታይዋን ጉዳይ በእሳት እንደመጫወት ነው” ሲሉ አሜሪካውን አቻቸው ያስጠነቀቁበት የቅርብ ጊዜ ንግግራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በታቃራኒው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን “የአሜሪካ ጦር ታይዋንን ከቻይና ወረራ ይከላከላል” ሲሉ መዛታቸው ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ቀውስ እንዳያስከትል ተሰግቷል፡፡