ታይዋን ወደ አየር መከላከያ ቀጠናዋ የገቡትን የቻይና አውሮፕላኖች ለማስጠንቀቅ ጄቶች ላከች
የታይዋን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዉ "ታይዋን ሉዓላዊነቷን ለትልቅ ጉልበተኛ የምትሰጥበት ምንም አይነት መንገድ የለም"ብለዋል
በጉዳዩ ላይ ምላሽ ያልሰጠቸው ቤጂንግ ከዚህ በፊት በሰጠችው መግለጫ “ሉዓላዊነቴን ለማስጠበቅ የማደርገው ልምምድ ነው” ማለቷ ይታወሳል
ታይዋን ወደ አየር መከላከያ ቀጠናዋ የገቡትን 29 የቻይና አውሮፕላኖች ለማስጠንቀቅ ጄቶች ላከች፡፡
ቻይና በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና ስትልክ እንደቆየች ታይዋን በተለያዩ ጊዜያት ስትከስ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡
ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች፣ የጸረ-ሰርጓጅ መርከብና ቅድመ ማስጠንቀቂያ አውሮፕላኖች በተለይም ከወርሃ ግንቦት መጨረሻ ወዲህ በታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና ሰማይ ስር ሲያንዣብቡ የሚታዩ የቻይና አውሮፕላኖች እንደሆኑም ጭምር ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ያም ሆኖ ሉዓላዊነቴ እስካልተደፈረ ድረስ የቻይና ድርጊት እታገሰዋለሁ ስትል የቆየችው ታይዋን፤ የቻይና አውሮፕላኖች በትናንትናው እለት የሀገሪቱን የአየር መከላከያ ቀጠና ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ኩፉኛ እንደተቆጣችና ለዚህም ማስጠንቀቅያ ለመስጠት ጄቶች መላኳ እየተነገረ ነው፡፡
ቻይና በትናንትናው እለት 17 ተዋጊዎች እና 6 ኤች-6 ቦምብ አውሮፕላኖች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ጦርነት፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ጸረ-ሰርጓጅ መርከቦች እና የአየር ላይ ነዳጅ ማደያ አውሮፕላኖችን የታዩበት ወታደራዊ ተልእኮ በታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና ሰማይ ስር ማከናወኗ፤ የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ባቀረበው ካርታ መሰረት የጦር አውሮፕላኖቹ "ፓራታስ" ተብሎ በሚታወቀውና የአየር መከላከያ ስፍራ በሆነው የታይዋን ሰሜን ምስራቅ ክፍል አካባቢ በረዋል፡፡
ቦምብ የታጠቁትና ኤሌክተሮኒክ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አውሮፕላኖቹ በታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና ባንዣበቡበት ወቅት በመረጃ መሰብሰቢያ አውሮፕላኖች ታጅበው እንደነበርም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
“በድረጊቱ የተቆጣቸው ታይዋን የቻይና አውሮፕላኖች ለማስጠንቀቅ የውጊያ አውሮፕላኖችን ልካለች”ም ነው ያለው ሚኒሰቴሩ፡፡
የትናንትናው እለት የቻይና ድርጊት (የታይዋን የአየር መከላከያ ጥሶ መግባት) በታይፒ እና ቤጂንግ መካከል ያለውን ውጥረት ይብልጥ እንዳያባብሰውም ተሰግቷል፡፡
ታይዋን ይህን ትበል እንጅ በቻይና በኩል እስካሁን ተባለ ነገር የለም፡፡
ቤጂንግ ከዚህ በፊት በሰጠችው መግለጫ “ሉዓላዊነቴን ለማስጠበቅ የማደርገው ልምምድ ነው” ማለቷ ይታወሳል፡፡
የታይዋን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዉ ግን በቻይና ጦር ሰራዊት የተካሄደው መጠነ ሰፊ ልምምድ የቻይናን ወታደራዊ ስጋት “ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ መሆኑን ያሳያል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዉ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "ታይዋን ሉዓላዊነቷን እና ዲሞክራሲዋን ለትልቅ ጉልበተኛ የምትሰጥበት ምንም አይነት መንገድ የለም፤ እድል አይደለም!" ሲሉም ተናገርዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለሮይተርስ በኢሜል እንደገለጹት ቤጂንግ በታይዋን ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ማስፈራራት ማቆም አለባባት ብለዋል፡፡
ታይዋንን እንደ አንድ ለመገንጠል ጫፍ ላይ እንዳለች የግዛት አካሏ አድርጋ የምትመለከተው ቻይና፤ አስፈላጊ ከሆነ በጉልበትም ልትመልሳት እንደምትችል በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እናም አሁን የምታደርጋቸው ተደጋጋሚ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ታይዋን ነጻነቷን ከማወጅ እንድትቆጠብ የሚያስጠነቅቅ እንዲሁም የታይዋን ምላሾችን ለመፈተሽ ታስቦ የተዘጋጀ ጦርነት መሆኑ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ጆ-ባይደን ባሳለፍነው ወርሃ ግንቦት በእስያ ባደረጉት ጉብኝት የሀገራት የአየር ክልሎችን ስለመጣስ ጉዳይ አንስተው መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቻይና "ለታይዋን በጣም ተጠግታ የምታደርገው በረራ አደጋ ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየትም ነበር የሰነዘሩት፡፡
ቻይና በታይዋን ላይ ወረራ ከፈጸመች፤ አሜሪካ ወታደራዊ አጸፋ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ መናራቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ቻይና በበኩሏ በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደርና ውጊያ መግጠም ካለባትም ለመግጠም ዝግጁ መሆኗን አሜሪካን ከሳምንት በፊት በመከላከያ ሚኒስትሯ ዌዪ ፈንጊሄ በኩል ማስጠንቀቋ አይዘነጋም፡፡
የቻይናው መከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ፤ ከአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎልዩድ አውስቲን ጋር ከኢስያ የደህንነት ጉባዔ ጎን ለጎን ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት፤ ታይዋንን ከቻይና መገንጠል የቻይና ወታደር “ማንኛውንም አይነት ዋጋ በመክፈል ከመዋጋት ውጭ ምርጫ እንዳይኖረው ያደርጋል” ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡
“ህዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር” በመባል የሚጠራው የቻይና ጦር የሀገሩን ብሔራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከማስጠበቅ በቀር ሌላ ምርጫ እንደማይኖረውም ሚኒስትሩ በወቅቱ አሜሪካን አስስበዋል፡፡