ታይዋን በበኩሏ የታይዋንን ቀጣይ ሁኔታ የሚወስኑት ቻይና ሳትሆን የታይዋን ዜጎች ብቻ ናቸው ብላለች
ታይዋን ከቻይና ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።
ቻይና ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትል ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ታይዋን ሉዓላዊ ሀገር እንድትሆን ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት፡፡
ይሄንን ተከትሎም ሁለቱ ሀገራት በየጊዜ እርስ በርሳቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ ሲሆኑ ከሰሞኑ በሲንጋፖር በተካሄደው የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በመከሩበት ወቅት ቻይና በታይዋን ጉዳይ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዘግጁ መሆኗን ለአሜሪካ ተናግራለች።
ይሄንን ተከትሎም የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ ዌን፤ ከቻይና ጋር ተባብረው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
እንደ ፕሬዝዳንቷ ገለጻ እኩልነት እስካለ ድረስ እና ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ እስካልቀረበ ድረስ ታይዋን ከቻይና ጋር ተቀራርባ መስራት ትፈልጋለች ሲሉ ተናግረዋል።
የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ለአሜሪካ አቻቸው ቻይና ከታይዋን ጋር ሰላማዊ ውህደትን መፈጸም ትፈልጋለች ያሉ ሲሆን ለጊዜው ከዚህ ውጪ ቻይና ሌላ እቅድ እንደሌላትም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ሳይ ቻይና ታይዋንን መቀላቀል ትፈልጋለች ነገር ግን ይህን ውሳኔ መወሰን ያለባቸው የታይዋን ዜጎች ብቻ ናቸው ስትልም ገልጻለች።
የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ ከአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎልዩድ አውስቲን ጋር ከኢስያ የደህንነት ጉባዔ ጎን ለጎን ከትናንት በስቲያ በሲንጋፖር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የቻይና መከላከያ ሚ/ር በዚህ መድረክ ላይ “ታይዋንን ከሀገሯ ለመነጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ወደ ጦርነት የስገባናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቻይና በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደርና ውጊያ መግጠም ካለባትም ለመግጠም ዝግጁ መሆኗን በመግለፅ ቤጂንግ አሜሪካን አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎልዩድ አውስቲን በበኩላቸው “ቻይና በታይዋን አካባቢ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ግጭት ቀስቃሽ አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ናቸው” ማለታቸው ተሰምቷል።
የቻይና የጦር አውሮፐላኖች በየቀኑ በታይዋን ደሴት አካባቢ የሚያደርጉት በረራዎች እና እንቅስቃሴዎች የቸካባውን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉም ተናግረዋል።