ቻይና በታይዋን አካባቢ የውጊያ ዝግጁነት ልምምድ ማድረጓን አስታወቀች
የባህር ኃይልና አየር ኃይል በጋራ የውጊያ ዝግጁነት ልምምድ ማድረጋቸውን የቻይና ጦር አስታወቀ
የውጊያ ዝግጁነት ልምምድ አሜሪካና ታይዋን በቅርቡ በጥምረት እያደረጉ ላለው እንቅስቃሴ በቂ ምለሽ ለመስጠት ነው
“ህዝባዊ የነጻነት ጦር” ተብሎ የሚጠራው የቻይና ጦር የምስራቃዊ እዝ በታይዋን ዙሪያ የውጊያ ዝግጁነት ልምምዶችን ማካሄዱ ተገለፀ።
የቻይና ጦር የምስራቃዊ እዝ በታይዋን አካባባቢ ያደረገው የውጊያ ዝግጁነት በውሃ ላይ እና በአየር ላይ የተካሄደ መሆኑንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የወታደራዊ እዙ ቃል አቀባይ ከፍተኛ ኮሎኔል ሺ ዪ በሰጡት መግለጫ፤ የውጊያ ዝግጁነት ልምምዱ የተካሄደው አሜሪካና ታይዋን በቅርቡ በጥምረት እያደረጉ ላለው እንቅስቃሴ በቂ ምለሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።
“አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታይዋን ላይ የተለያየ አቋም እያንጸባረቀች ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “የአሜሪካ እንቅስቃሴ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለታይዋን ነጻት ድጋፍ ለማድረግ ነው፤ ይህ ደግሞ ታይዋንን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከታት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ታይዋን የቻይና አንድ አካል ነች” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “ቻይና ጦር ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት መቀልበስ በሚችልበት መልኩ የማጠናከሪያ ልምምዶችን ማድረጉን ይቀጥላል” ብለዋል።
“ታይዋንን ነጻ ሀገር እናደርጋለን የሚሉ ገንጣዮችን እንሰብራለን” ሲሉም ኮሎኔል ሺ ዪ ተናግረለዋል።
ቻይና ባሳለፍነው ሳምንትም “ለአሜሪካ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው” ያለችውን ወታደራዊ ልምምድ በታይዋን አቅራቢያ ማድረጓ ይታወሳል።
ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ቻይና በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር ጭምር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ስትገባ ይታያል።
ባሳለፍነው ሳምንት በእስያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኀገራቸው ታይዋንን ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል መናገራቸው ይታወሳል።
ባይደን ቻይና ታይዋንን በተመለከተ ኃይል የምትጠቀም ከሆነ እኛም መጠቀማችን አይቀርም ብለዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጅንፒንግ ከወራት በፊት ታይዋንን ከቻይና ጋር ለማዋሃድ መዛታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ለማዋሃድ ኃይል መጠቀም ስለማሰባቸው አልተናገሩም።
ታይዋን ነጻ ሀገር ነኝ የምትል ሲሆን፤ በአንጻሩ ቻይና ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ ትመለከታታለች።