ታይዋን ለእያንዳንዱ ዜጋዋ ገንዘብ ልትሰጥ ነው
ታይፒ 140 ቢሊየን የታይዋን ዶላር የመደበች ሲሆን፥ እያንዳንዱ ዜጋ 6 ሺህ የታይዋን ላር ይደርሰዋል ተብሏል
በታይዋን የምጣኔ ሀብት እድገት ለእያንዳንዱ ዜጋ እንዲደርስ የአዲስ አመት ስጦታ ተዘጋጅቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ቻንግ
ታይዋን አዲሱን አመት በማስመልከት ለእያንዳንዱ ዜጋዋ የድጎማ ገንዘብ ልትሰጥ ነው።
የደሴቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ቻንግ እንዳስታወቁት ለእያንዳንዱ ዜጋ 6 ሺህ የታይዋን ዶላር ለመስጠት ታቅዷል።
ለዚህም 140 ቢሊየን የታይዋን ዶላር የተመደበ ሲሆንበፓርላማ ከጸደቀ በኋላ ተፈጻሚ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘቡ በምን መልኩ ለዜጎች እንደሚደርስ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ኢኮኖሚዋ በወጪ ንግድ ላይ የተመሰረተው ታይዋን፥ በ2021 የ6 ነጥብ 45 በመቶ እድገት አስመዝግባለች።
ኢኮኖሚዋ በ2022 እና 2023 የምታስመዘግበው እድገት እንደሚቀንስ ቢገመትም፥ በ2022 ከግብር የሰበሰበችው ገንዘብ 380 ቢሊየን የታይዋን ዶላር (12 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር) መድረሱን ሮይተርስ።
ይህም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የገጠመውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማርገብ እንዳገዛትና በኤሌክትሪክ እና የጤና መድህን ላይ ድጎማ እንድታደርግ አግዟታል።
በኢኮኖሚዋ የታየውን እምርታ ለሁሉም ዜጎች በማከፋፈል ማሳየት አስፈልጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ቻንግ፥ የአዲሱ አመት ስጦታ ገዥው ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ በተቆጣጠረው ፓርላማ መጽደቅ ይኖርበታል ብለዋል።
ቻይና የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትላት ታይዋን ከስማርት ስልኮች እስከ ተዋጊ ጄቶች ግብአትነት የሚውሉ ኮንዳክተሮች ቀዳሚዋ አማራች መሆኑ ይታወቃል።
ኮቪድ 19 በአለም ዙሪያ በርካቶችን በቤታቸው ውስጥ ስራቸውን እንዲከውኑ ሲያስገድድ ታይፒ የምርቶቿ ገበያ ደርቶላት ነበር።
ይህም በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ ሀገራት ሲንገዳገዱ ታይዋን በእድገት እንድትቀጥል አድርጓታል ነው የተባለው።
የታይዋን ማዕከላዊ ባንክ በመስከረም ወር 2022 ያወጣውን የ3 ነጥብ 51 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ግምት በታህሳስ ወር ወደ 2 ነጥብ 91 በመቶ ዝቅ ቢያደርገውም ደሴቷ እያስመዘገብች ያለው እድገት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ይህን እድገትም ለእያንዳንዱ ዜጋ 6 ሺህ የታይዋን ዶላር (200 የአሜሪካ ዶላር) በመስጠት ለማሳየት አቅዳለች።
አንድ የአሜሪካ ዶላር በ30 ነጥብ 67 የታይዋን ዶላር ይመነዘራል።