አሜሪካ ለታይዋን 180 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ ተስማማች
ስምምነቱ ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከተውን ቻይናን ያስቆጣል ተብሏል
ስምምነቱ የአሜሪካን ብሄራዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ እና የደህንነት ጥቅሞችን እንደሚያስከብር ፔንታጎን ገልጿል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በታይፔ እና በዋሽንግተን መካከል በተደረገው የቅርብ ጊዜ የጦር መሳሪያ ስምምነት ለታይዋን ጸረ-ታንክ ስርዓትን በ180 ሚሊዮን ዶላር መሸጥን አጽድቋል።
ፔንታጎን ታይዋን የቮልካኖ ጸረ-ታንክ ስርዓቶች፣ የጭነት መኪናዎች ፣ ጥይቶችን እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ክፍሎች እንደሚደርሳት አስታውቋል ።
ፔንታጎን እንደተናገረው ይህ ስምምነት ታይዋን የጦር ኃይሏን ለማዘመን እና የተቀናጀ የመከላከያ አቅምን ለማዳበር የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የአሜሪካን ብሄራዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ እና የደህንነት ጥቅሞችን እንደሚያስከብር ገልጿል።
ስምምነቱ ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከተውን ቻይናን ያስቆጣል ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2022 መጀመሪያ ላይ ቻይና የምዕራባውያን እና የአሜሪካ ፖለቲከኞች በታይዋን ላደረጉት ጉብኝት በቁጣ ምላሽ ሰጥታለች።
ባለፈው ነሃሴ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፖሎሲ ያደረጉትን ጉብኝት በመቃወም ወታደራዊ ልምምዶችን ያደረገች ሲሆን፤ ጉብኝቱ ለዓመታት አልታየም የተባለውን የሀገራቱ ውጥረቱ እንዲባባስ አድርጓል። .
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለታይዋን 10 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ የሚሰጥ የመከላከያ ወጪ አዋጅን የፈረሙ ሲሆን፤ አዋጁ እ.አ.አ እስከ 2027 ድረስ ለታይዋን 2 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ እርዳታን ይፈቅዳል ተብሏል።
ቤጂንግ በዚህ ህግ ላይ አስተያየት ስትሰጥ አሜሪካ በቻይና ላይ አሉታዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የብሔራዊ መከላከያ ፍቃድ ህግን መጠቀሟን በጥብቅ እንደምትቃወም ተናግራለች።