ታይዋን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጊዜን ልታራዝም ነው
ፕሬዝደንት ሳይ ኢንግ ዌን በጉዳዩ ላይ ለመወያየት የታይዋንን ብሄራዊ ደህንነት ኮሚቴ ስብሰባ ጠርተዋል
ታይዋን፤ አራት ወራት ብቻ የነበረውን ብሔራዊ አገልግሎት ወደ አንድ አመት ለማራዘም አቅዳለች
የቻይና የፈረጠመ ጡንቻ ያሰጋት ታይዋን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን ጊዜ ልታራዝም መሆኑ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ገለጹ፡፡
የታይዋን ፕሬዝደንት ሳይ ኢንግ ዌን በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ዛሬ ማክሰኞ የደሴቷን የሲቪል መከላከያ ማጠናከር ላይ ለመወያየት ብሔራዊ የደህንነት ኮሚቴ ስብሰባ መጥራታቸውንም ጭምር ተናግረዋል ባለስልጣኑ፡፡
እንደ ባለስልጣኑ ገለጻ ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ የፕሬዝዳንተዋ የደህንነት ቡድን ከ 2020 ጀምሮ ያለውን የታይዋን ወታደራዊ ቁመና እየገመገመ ነው ፡፡
ባለስልጣኑ ይህን ይበሉ እንጅ በጉዳዩ ላይ የተጠየቀው የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቤጂንግን የታይዋን የሉዓላዊነት ይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ያደረገችው ታይፔ የቻይና የወቅቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እጅጉን ያሰጋት ይመስላል፡፡
በተለይም በትናንትነው እለት 71 የቻይና አውሮፕላኖች የታዩበት ልምምድ ማድረጓንና ከነዚህም 47ቱ በደሴቷ የአየር መከላከያ መለያ ዞን ውስጥ ተሻግረው መግባታቸው እጅጉን እንዳስደነገጣትም መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
በከፍተኛ ደረጃ የደህንነት ውይይቱ ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉት ባለስልጣን "የቻይና የተለያዩ የተናጠል ድርጊቶች ለቀጠናው ደህንነት ትልቅ ስጋት ሆኗል" ብለዋል፡፡
ታይዋን ይህን ሁሉ የቻይና እብደት ቁጭ ብላ እንደማትመለከት የገለጹት ባለስልጣኑ፤ አራት ወራት ብቻ የነበረው ብሔራዊ አገልግሎት ወደ አንድ አመት ለማራዘም እቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2024 ተግባራዊ በሚሆነው እቅድ መሰረት ፤ ሰልጣኞች የተኩስ ልምምዶችን ጨምሮ የአሜሪካ ኃይሎች የሚጠቀሙባቸውን የውጊያ መመሪያዎች እንዲያውቁና የጸረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎችን እንዲሁም ጸረ-ታንክ ሚሳኤሎችን ዙሪያ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያስችል ስልጠና ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
ወታደራዊ ሰልጣኞቹ ቻይና ለመውረር በምትሞክርበት ማንኛውም ሰአት መደበኛ ሃይሎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ በማስቻል ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።
የብሔራዊ ፖሊሲ ፋውንዴሽን ተመራማሪ የሆኑት ቺህ ቹንግ አገልግሎቱ መራዘሙ በየአመቱ ከ60 እስከ 70 ሺህ የሚሆን ኃይል ለመጨመር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የሚጨመረው የሰው ኃይል አሁን ካለው የ165 ሺህ የፕሮፌሽናል ሃይል ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡