የታይዋን የሚሳዔል ማምረቻ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆቴል ውስጥ ሞተው ተገኙ
የሀገሪቱ መርማሪ ፖሊስ የኦው ያንግ የሞቱበትን ምክንያት በማጣራት ላይ መሆኑ አስታውቋል
የታይዋን መከላከያ ሚኒሰቴር “ኦው ያንግ የታይዋን የሚሳዔል የማምረት አቅምን ለማሳደግ ሲሰሩ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው”ብሏል
የታይዋን የሚሳዔል ማምረቻ ከፍተኛ ተመራማሪና በወታደራዊ ባለቤትነት የተያዘው የናሽናል ቹንግ-ሻን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ምክትል ኃላፊ ኦው ያንግ ሊ-ህሲንግ ፤ ሆቴል ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
እንደ የታይዋኑ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ ዘገባ ከሆነ ኦው ያንግ ሊ-ህሲንግ ሞተው የተገኙው በደቡባዊ ታይዋን በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ነው፡፡
ከቤተሰቦቹ በተገኘ መረጃ መሰረት የ57 አመቱ ኦው ያንግ የሞት ምክንያት የልብ ድካም ሊሆን እንደሚችል ቢገለጽም፤ የሀገሪቱ መርማሪ ፖሊስ ትክክለኛው የሞት ምክንያት ለማወቅ አስፈላጊውን የማጣራት ሂደት ላይ መሆኑ አስታውቋል፡፡
ኦው ያንግ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ የተለያዩ የሚሳዔል ማምረቻ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል በሚል ወደ ሃላፊነት የመጡ እንዲሁም ወደ ሃላፊነት ከመጡ ወዲህ የታይዋን የሚሳዔል የማምረት አቅምን ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩ ከፍተኛ ባለሙያ እንደነበሩ የታይዋን መከላከያ ሚኒሰቴር መረጃ ያስረዳል፡፡
ታይና ከቻይና ሊቃጣባት የሚችለውን አደጋ ለመከላከል በሚል ሚሳዔልን በከፍተኛ ሁኔታ በማምረት ላይ ተጠምዳለች፡፡ በዚህ አመት ብቻ የሚሳዔል ማምረት አቅሟን ወደ 500 ለማሳደግ እየሰራች መሆኗም ይገለጻል፡፡
የወቅቱ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ተከትሎ ቻይና እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷ፤ የታይዋን መሪዎች ነገሮች በቅርበት እንዲከታተሉ ያስገደደና ሁኔታ መፈጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም አሁን ላይ የናንሲ ፔሎሲ ጉብኝት ተከትሎ ቻይና በምታደርገው የአየር ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በሩቅ ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን ታይዋን ከፍተኛ የውጊያ ጥንቃቄ እንዳወጀች ነው፡፡
የታይዋን ፕሬዝደንት ጻይ ኢንግ ዌን ሀገራቸው ማንንም እንደማትተነኩስና ነገርግን ራሷን እንደምትከላከል መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የቻይና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለታይዋን ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲም ነበር የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ፡፡