የናንሲ ፔሎሲን ጉዞ ተከትሎ በቻይና-ታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ስታራምድ የቆየችውን የ"አንድ ቻይና” ፖሊሲ አቋሟን እንዳጸናች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ከወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ያሳስቧታል ብለዋል።
ሰሞኑን በቻይና-ታይዋን ጉዳይ የተከሰተውን ውጥረት በትኩረት እየተከታተለች መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የ“አንድ ቻይና” ፖሊሲ አቋም ዛሬ የተጀመረ አይደለም ያሉት አምባሳደር መለስ፥ "ከቻይና ጋር በነበረን ግንኙነት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስታት አፅንተው የያዙት አቋም ነው" ብለዋል።
አሁንም ኢትዮጵያ ለ“አንድ ቻይና” ፖሊሲ ፅኑ አቋም አላት ያሉም ሲሆን፥ ፖሊሲውን ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረትም እንደሚያራምዱት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው አምባሳደር መለስ ያነሱት።
የቻይና የመከላከያ ሰራዊት የተመሰረተበትን 95ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የቻይና የመከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት፣ ጸጥታና ጥቅም ከማስከበር አልፎ ለዓለማችን ሰላምና መረጋጋት እያደረገ ላለው በጎ ሚና ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲን የቻይናን ዛቻ ወደ ጎን በመተው ወደ ታይዋን መጓዛቸውን ተከትሎ በቻይና-ታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል።
ቻይና አሜሪካ በዴሞክራሲ ሽፋን ሉአላዊነቴን ተዳፍራለች ያለች ሲሆን፤ ቻይናን የሚዳፈሩ ሁሉ ይቀጣሉ ማለቷ አይዘነጋም።
የቻይና ጦር የፔሎሲን ጉብኝት ተከትሎ የአጸፋ እርጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ በትናንትናው እለትም 27 የቻይና የጦር ጄቶች የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው ገብተዋል።
ሩሲያ፣ ሰሜን ከሮያ እና ኤርትራ ቻይናን በመደገፍ አቋማቸውን ያንፀባረቁ ሲሆን፤ ኤርትራ የፔሎሲን ጉብኝት ህግን የጣሰ ነው ስትልም ተችታለች።