ታክስ የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ(ሳድክ) ዋና ጸሃፊ ሆነው ያገለገሉ ናቸው
የታንዛንያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን ሰቴርጎሜና ላውረንስ ታክስን በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመርያ ሴት የመከላከያ ሚኒሰትር አድርገው ሾሙ፡፡
በዘህም ሰቴርጎሜና ላውረንስ ታክስ በነሃሴ ወር መጀመርያወቹ ህይታቸው ያለፈውን ኤልያስ ክዋንዲክዋን እንደሚተኩ የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አስታውቋል ሲል ሺንዋ ዘግቧል፡፡
ከታንዛንያ ነጻነት ወዲህ የሚጀመርያ ሴት መከላከያ ሚኒሰትር ሆነው የተሸሙት ታክስ፤ ቀደም ሲል እንደፈረንጆቹ 1992 የቀጠናው ሀገራት ፖለቲካዊ፣ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና የጸጥታ ትብብርና ውህደት ለማሳደግ በሚል የተቋቀመው የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ(ሳድክ) የመጀመርያዋና ብቸኛዋ ዋና ጸሃፊ ሆነው አገልግሏል፡፡
ታክስ በሳድክ የነበራቸው የሃላፊነት አገልግሎት ጊዜ ከቀናት በፊት እንደፈረንጆቹ ነሃሴ 31/2021 ማብቃቱንም ነው የተገለጸው፡፡
ሳሚያ ሱሉሁ የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ሴት በመሆናቸው ብቻ በርካቶች ' ሀገር መምራት አይችሉም' ሲሉ እንደነበር ባለፉት ጊዝያት መግለጻቸው ይተዋሳል፡፡
አንዳንድ ሰዎች "ሴቶች የተሻሉ መሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አያውቁም ፤ ልንመራና ልናሳያቸው ግን እዚህ ተሰይመናል"በማለት ሳሚያ ከበቢሲ ጋር በነበራቸው ገልጸው ነበር፡፡
ሳሚያ ለትችቶች ምላሽ ለመስጠት የልማት ግቦች ማስቀደምና የህዝብን ፍላጎት ከግምት ማስገባት ብቻ በቂ እንደሆነና እንደሚያምኑም ነው የተናገሩት፡፡ሌሎች ሀገራትም በሴቶች ከተመሩ እንደነ ላይቤርያ እና ማእከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ከመሳሰሉ ሀገራት ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሳሚያ ታክስን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው ሴት በመሆናቸው ብቻ ሲያጋጥሟቸው የነበሩ ፈተናዋች ከማቃለል እና ሴቶች መምራት እንደሚችሉ ከማሳየት አንጸር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በርካቶች እያነሱ ነው፡፡
ሳሚያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን ህልፈት ተከትሎ እንደ ጎርጎሮሲያን ዘመን በመጋቢት ወር 2021 በትረ ስልጣን መጨበጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህም ላለፉት 7 ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩትን የ61 ዓመቷን አዛውንት ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡