ኢትዮጵያዊው አትሌት ደራራ “በጫማው ምክንያት” አሸናፊነቱን ተነጠቀ
ደራራ በቬይና ሲቲ ማራቶን 02፡09፡22 በሆነ ሰዓት ሮጦ ነበር ውድድሩን የጨረሰው
ውድደሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ኬንያዊው ሊዮናርድ ላንጋት አሸናፊ ሆኗል
ኢትዮጵያዊው አትሌት ደራራ ሁሪሳ በቬና ሲቲ ማራቶን በአንደኛነት ቢያጠናቅም “በጫማው ምክንያት” አሸናፊነቱን ተነጥቋል፡፡
በትላንትናው ዕለት የቬይና ሲቲ ማራቶን 02፡09፡22 በሆነ ሰዓት ሮጦ ውድድሩን በአንደኝነት የጨረሰው ኢትዮጵያዊው አትሌት ደራራ በጫማው ምክንያት አሸናፊነቱን ተቀምቷል፡፡
አትሌቱ አሸናፊነቱን የተነጠቀው “ጫማህ የውድድሩን ህግ አያሟላም” በሚል ነው፡፡ ይህም የሆነው የጫማው ሶል ሲለካ አምስት ሴንቲ ሜትር( ለውድድሩ ከተፈቀደው የጫማ ሶል በአንድ ሳንቲ ሜትር የሚበልጥ) በመሆኑ ነው ተብለዋል፡፡
የሩጫው አዘጋጅ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መረጃ “የዛሬው የቬይና ማራቶን ውድድር አሸናፊ ኢትዮጵያዊው ደራራ ሁሪሳ የነበረ ቢሆንም ያደረገው ጫማ ህጉን ባለማሟላቱላ ያስመዘገበው ውጤት ተሰርዞበታል፡፡
አትሌት ደራራ የገባበት ሰአት 02፡09፡22 ቢሆንም ለውድድሩ ከአራት ሳንቲ ሜትር የሚበልጥ ሶል ያለው ጫማ ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ የእሱ ጫማ ግን አምስት ሆኖ ተገኝቷል” ብሏል፡፡
“ውድደሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ኬንያዊው ሊዮናርድ ላንጋት አሸናፊ መሆኑን አስታውቋል”ም ነው ያለው የሩጫው አዘጋጅ፡፡
የ24 ዓመቱ አትሌት ደራራ ባለፈው አመት በሙምባይ ማራቶን የቦታውን ሪከርድ መስበሩ የሚታወስ ነው፡፡የመሮጫ ጫማ ጉዳይ በአለም አቀፍ አትሌቲክስ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡