የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር መጽሃፍትን በሶፍት ኮፒ ለአንባቢያን ማድረስ ሊጀምር መሆኑን ገለጸ
አንባቢ ትውልድ መፍጠር ካልተቻለ ኢትዮጵያ መቼም ከችግሯ እንደማትወጣም ማህበሩ አስታውቋል
ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር የተዳረገቸው አንባቢ ትውልድ ባለመፈጠሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ገልጿል
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር መጸሀፍትን በሶፍት ኮፒ ለአንባቢያን የማድረስ እቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት እና ደራሲ አበረ አዳሙ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት “ጠያቂ እና ለችግሮች መፍትሔ የሚፈልግ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም” ብለዋል።
ማንበብ የሁሉ ነገር መሰረት ነው የሚሉት ደራሲ አበረ ባለፉት ዓመታት አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ባለመሰራቱ አሁን ላለንበት ችግር ተዳርገናል ይላሉ።
“በደርግ የአስተዳድር ጊዜ ወታደሩ፤ከተሜው እና ሌላውም ማህበረሰብ በማንበብ ይዝናና ነበር” ያሉት ፕሬዘዳንቱ “አሁን መጻፍ እና ማንበብ የሚችሉ ዜጎች፤የትምህርት ቤቶች፤የዩንቨርሲቲዎች እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ቁጥራቸው ቢጨምርም ለማወቅ እና ለመዝናናት መጽሀፍትን የሚያነብ ትውልድ በዚያው መጠን ቀንሷል ብለዋል።
አሁን ካለው የአስተዳድር ስርዓት በፊት በነበረው ጊዜ የአንድ መጽሀፍ ህትመት በትንሹ 30 ሺህ ነበር ፤አሁን ላይ ግን የአንድ መጽሀፍ ኮፒ ከአምስት ሺህ አይበልጥም ይህ የሆነው ደግሞ አንባቢ በመጥፋቱ ምክንያት እንደሆነ ደራሲ አበረ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ቤተ መጽሀፍት የሌለበት የለም ነገር ግን አንባቢ ስለሌላቸው መጽሃፍቱ የሸረሪት ድር አድርቶባቸዋል፤ ካፌዎች እና ጃንቦ ቤቶች ግን በሰው ተጥለቅልቀው መፈናፈኛ ቦታ የላቸውም ሲሉም ደራሲ አበረ ገልጸዋል።
“አንባቢ ትውልድ ባለመፈጠሩ ምክንያት ይሄንን አድርግ ሲባል ለምን? ከማለት ይልቅ አብሮት የሚማረውን፤የሚኖረውን ወንድሙን እየገደለ እና እያፈናቀለ ነው” ሲሉም አክለዋል።
እየመጣ ያለው ትውልድ ሰውን ከመግደል አልፎ እንስሳትን ሳይቀር እየገደለ ያለ ነው የሚሉት ፕሬዘዳንቱ ከችግራችን እንድንወጣ የማንበብ አብዮት ያስፈልገናል ሲሉም አክለዋል።
ደራሲ አበረ አክለውም በየጊዜው የህትመት ዋጋ መጨመር፤ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በየጊዜው መዘመን፤የማህበራዊ ትስስር ገጾች መስፋፋት እና የኪፒ ራይት ችግሮች ለድርሰት ኢንዱስትሪው አለማደግ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂዎች የበለጠ በዘመኑ ቁጥር ለድርሰት ኢንዱስትሪው ፈተና ብቻ ሳይሆኑ አድልም በመሆኑ ዘርፉን ለመጠቀም እየሰሩ መሆኑንም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።
ዓመታት የተፈጀባቸው የደራሲያን ስራዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በህገወጥ መንገድ መጽሀፍትን ማሰራጨት፤መጽሀፍ አታሚዎች ያለደራሲው ፈቃድ ማተም፤መጽሀፍ አዟሪዎች ከደራሲው አውቅና ውጪ የራሳቸውን ዋጋ እየለጠፉ መሸጥ እና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ደራሲ አበረ ተናግረዋል።
የደራሲያን ማህበር በራሱ መንገድ እየተንቀሳቀሰ አጥፊዎችን በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደራሲ አበረ አንባቢዎች መጽሀፍትን ሲገዙ ዋጋው የተፋቀ ወይም የታተመ መሆኑን በአንክሮ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መጽሀፍትን ለአንባቢዎች በቀላሉ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከሶፍትዌር አበልጻጊዎች ጋር በመስራት ላይ መሆናቸውን ደራሲ አበረ ገልጸዋል።
ማህበሩ አንባቢዎች የታተመ መጽሀፍትን እንዲያነቡ ቢያበረታታም ቴክኖሎጂዎች ችግር ብቻ ሳይሆን አድሎችንም ይዘው ስለሚመጡ መጽሀፍትን በሶፍት ኮፒ እንዲደርሳቸው እናደርጋለን ሲሉም ፕሬዘዳንት ደራሲ አበረ ጠቁመዋል።
የኢትይጵያ ደራሲያን ማህበር ከ61 ዓመት በፊት የደራሲያንን ጥቅም ለማስከበር የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ የሙያ ማህበር ነው።