ከተማሪዋ ያረገዘችው መምህር በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰሰች
መምህሯ ከ17 ዓመት ተማሪዋ ልጅ መውለዷ ተገልጿል
የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈጸመበት ተማሪ የስነ ልቦና ድጋፍ እየተደረገለት ነው ተብሏል
ከተማሪዋ ያረገዘችው መምህር በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሰሰች።
የ33 ዓመት እድሜ አላት የተባለችው መምህር አሜሪካዊ ስትሆን ከተማሪዋ ልጅ መውለዷ ተገልጿል።
መምህር ሞርጋን ፍሬች የ17 ዓመት እድሜ ካለው ተማሪዋ ጋር ጾታዊ ግንኙነት ፈጽማለች የተባለ ሲሆን ይህም የሀገሪቱን ህግ ተላልፋ ተገኝታለች ተብሏል።
መምህርቷ 18 ዓመት ባልሞላው ተማሪዋ ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽማለች የተባለ ሲሆን ተማሪው የስነ ልቦና ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል።
ፖሊስ ጥቆማው ከሁለት ዓመት በፊት እንደደረሰው ገልጾ ምርመራው ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ በድብቅ ምርመራ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውቋል።
ጥቆማው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮም መምህርቷ በትምህርት ቤቱ የነበራትን ስራ በራሷ ፈቃድ መልቀቋም ተገልጿል።
የተማሪው ወላጆች በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በልጃቸው ጉዳይ ሀላፊነቱን እንዳልተወጣ መናገራቸው ተገልጿል።
ይሁንና ትምህርት ቤቱ ከህግ እና ከሙያ ስነ ምግባር ውጪ የሆኑ መምህራንን እንደማይታገስ ገልጾ መሰል ድርጊቶች ጥንቃቄ የሚጠይቁ መሆናቸውን አስታውቋል።