ለ20 አመታት በስራ ገበታቸው ያልተገኙት ጣሊያናዊት መምህርት በመጨረሻም ተባረዋል
የ51 አመቷ የታሪክና ፍልስፍና መምህርት በ24 አመት ውስጥ በክፍል ውስጥ የተገኙት ከ4 አመት አይበልጥም
መምህርቷ ከ100 በላይ ሰነዶችን በማቅረብ ከስራ መባረር የለብኝም ብለዋል
ጣሊያናዊቷ መምህርት ሲንዚያ ፓውሊና ዴሊዮ በቬነስ አካባቢ የተማሩ ሁሉ በዝናቸው ያውቋቸዋል።
የታሪክና ፍልስፍና መምህርቷ ለተማሪዎች በሚያስተላልፉት የካበተ እውቀት ግን አይደለም እውቅናቸው።
የ51 አመቷ ጎልማሳ መምህርት ወደ ትምህርት ቤት ብቅ ብሎ ለረጅም ጊዜ በመጥፋት ታዋቂነትን አትርፈዋል።
በክፍል ውስጥም ያለምንም ዝግጅት በመግባትና እንደነገሩ አስተምረው ፈትነው ያሻቸውን ውጤት በመስጠትም ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
በ24 አመት የመምህርነት የአገልግሎት ዘመናቸው ውስጥ በክፍል ውስጥ ተገኝተው ያስተማሩበትም ከ4 አመት አይበልጥም ተብሏል።
የተማሪዎች፣ ወላጆች እንዲሁም የትምህርት ቤት አስተዳደር ሰራተኞች ቅሬታ እጅግ ሲበዛም የጣሊያን ትምህርት ሚኒስቴር በፈረንጆቹ 2017 የዴሊዮን የስራ ውል መሰረዙን ላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ አውስቷል።
የታሪክ መምህርቷ ግን የሰነዶችን ዋጋ ያውቃሉና ከ100 በላይ ዶሴዎችን ይዘው ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይወስዱታል።
ዳሊዮ 67 የህክምና ፈቃድ፣ 16 ከግል ጉዳይ ጋር የተያያዘ ፈቃድ የጠየቁበት፣ 24 የአካል ጉዳት ያለባቸውን ቤተሰቦቼን ለመርዳት የሚሉ የፍቃድ ጥያቄዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰነዶችን በማስረጃነት አቅርበዋል።
የጣሊያን ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እነዚህን ዶሴዎች ተመልክቶ የሀገሪቱን ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ሽሮት ዴሊዮ ዳግም ወደ ስራ ይመለሳሉ።
መምህርቷ ዳግም ወደ ስራ ቢመለሱም የ20 አመት ልማዳቸው አልቀቃቸውም፤ አደጋ ገጠመኝ፣ ወልጃለሁ፣ ልጄን ማጥባት አለብኝ የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን እየደረደሩም የውሃ ሽታ ሆነው መጥፋታቸውን ቀጠሉ ይላል የጣሊያን ትምህርት ሚኒስቴር።
ባለሙያዎች በክፍል ውስጥ ባደረጉት ግምገማም መምህርቷ ምንም አይነት ዝግጅት ሳያደርጉ የሚገቡ መሆናቸውንና ለ20 አመት የሚጠጋ ጊዜ በስራ ገበታቸው እንዳልነበሩ በማረጋገጥ ለመጨረሻ ጊዜ ከስራቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።
ሲንዚያ ፓውሊና ዴሊዮ ግን “ለሁለት አስርት ከትምህርት ቤት አልቀረሁም፤ ሰነዶቼን አቅርቤ መከራከሬ አይቀርም” ሲሉ ለጣሊያኑ ተነባቢ ጋዜጣ ላ ሪፐብሊካ ተናግረዋል።