ሰዋሂሊ ቋንቋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት በስፋት ይነገራል
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የሰዋሂሊ ቋንቋ መምህራን ከታንዛኒያ እንዲመጡላት መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት በሩዋንዳ ጉብኝት ላይ ለነበሩት የታንዛኒያዋ አቻቸው ሳሚያ ሱሁሉ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፖል ካጋሜ ፤ ሀገራቸው የሰዋሂሊ ትምህርት መጀመሯን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ጆን ማጉፉሊን በመተካት የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ለሆኑት ሳሚያ ሱሁሉ መናገራቸውም ነው የተዘገበው።
እ.አ.አ በ 2017 ሩዋንዳ ሰዋሂሊ ቋንቋን ከፈረንሳይኛ እና ከእንግሊዝኛ በመቀጠል አራተኛ ይፋዊ ቋንቋ በማድረግ አጽድቃ ነበር። ይሁን እንጅ ሰዋሂሊ ቋንቋ በመምህራን እጥረት ዕድገቱ ውስን ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል።
ቋንቋው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ይፋዊ የሥራ ቋንቋ ሲሆን ሩዋንዳ የዚህ አባል ናት።
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ከሳምንታት በፊት የአፍሪካ ውህደት ቀን ሲታሰብ አፍሪካውያን ሰዋሂሊ ቋንቋን በመማር ለአህጉሪቱ ውህደት ጥረት እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሰዋሂሊ ቋንቋ በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ሩዋንዳ፣ቡሩንዲ እና በሌሎች ሀገሮች የሚነገር ቋንቋ ሲሆን እስከ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት በስፋት ይነገራል።
ሰዋሂሊ ቋንቋ ከአረብኛ፣ እንግሊዝኛ ፣ፈረንሳይኛ ፣ፖርቱጋልኛ፣ስፓኒሽ ጋር የአፍሪካ ሕብረት የሥራ ቋንቋ ሲሆን ብቸኛው አህጉር በቀል ቋንቋ ነው።