ግብጽ ተንቀሳቃሽ የዳንስ ምስል በፌስቡክ ገጿ ላይ የለቀቀችን የዩንቨርሲቲ መምህር ከስራ አገደች
ከስራ የታገዱት ፕሮፌሰር ሞና አል ፕሪንስ የስዊዝ ልንል ዩንቨርስቲ መምህር ነበሩ
መምህሯ ለተማሪዎቿ አርአያ አልሆኑም በሚል ነው ከስራ የተባረሩት
ግብጽ የዳንስ ቪዲዮ በፌስቡክ ገጿ ላይ የፖሰተችን የዩንቨርሲቲ መምህር ከስራ አገደች።
ፕሮፌሰር ሞና አል ፕሪንስ በመባል የሚታወቁት እኝህ እንስት ከሰሞኑ በግላቸው የፌስቡክ ገጽ ላይ በሆድ የሚጨፈር የሰውነት እንቅስቃሴ ወይም ቤሊ ዳንስ ለተከታዮቻቸው አጋርተው ነበር።
እኝህ የስዊዝ ልንል ዩንቨርስቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ግብጻውያን ሴቶች እና ወጣቶች በነጻነትን የሚፈልጉትን እንዲያደርጉ በማበረታታትም ይታወቃሉ።
በቅርቡ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ለተከታዮቻቸው ባጋሩት ተንቀሳቃሽ የዳንስ ምስል የግብጽን ባህል እና እምነት የሚጻረር ነው በሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
የግብጽ አስተዳድራዊ ፍርድ ቤትም መምህሯ ለተማሪዎቻቸው አርዓያ ያልሆነ እንቅስቃሴ አድርገዋል በሚል ከስራ እንዲታገዱ መወሰኑ ተገልጿል።
መምህር ሞና ለወጣቶች አርአያ ያልሆነ ተማሪዎችን ወዳልተፈለገ ድርጊት የሚመራ ተግባር እንደፈጸሙ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል ተብሏል።
መምህር ሞና ዳንስ ከፈለጉ መብታቸው ነው ያለው ፍርድ ቤቱ የግል ነጻነት ማለት ወጣቶች ልቅ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መገፋፋት ግን ወንጀል ነው ብሏል ተብሏል ።
ፕሮፌሰር ሞና አል ፕሪንስ በፈረንጆቹ 2018 ላይ በተካሄደው የግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ብቸኛዋ ሴት እጩ ተወዳዳሪ እንደነበሩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።