ቴሌግራም በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን መረጃ አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ
የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ስልክ ቁጥር ለህግ አካላት እንደሚሰጥ ዋና ስራ አስፈጻሚው ፓቨል ዱሮቭ ገልጿል
ቴሌግራም የሀሰተኛ መረጃ፣ የህጻናት ወሲብ ፊልም እና የሽብር ይዘቶች ማሰራጫ ሆኗል በሚል ይተቻል
ታዋቂው የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ቴሌግራም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን መረጃ ለህግ አካላት ለመስጠት ተስማማ።
ቴሌግራም ከዚህ ቀደም ይዞት የነበረውን የደንበኞቹን መረጃ ለሶስተኛ ወገን ያለማጋራት ፖሊሲ ለመለወጥ ተገዷል።
የመተግበሪያው ፈጣሪና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቨል ዱሮቭ፥ ኩባንያቸው ተጠርጣሪዎች የሚጠቀሙባቸውን ስልክ ቁጥሮች እና የመለያ አድራሻዎች (አይፒ) ለህግ አካላት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
“99.99 በመቶዎቹ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ከወንጀል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም፤ 0.001 በመቶ የሚሆኑት የሚፈጽሙት ያልተገባ ተግባር የቴሌግራምን ምስል እያጎደፈ 1 ቢሊየን የሚጠጉ ደንበኞቻችን ፍላጎት አደጋ ላይ ጥሏል” ሲሉም ነው የገለጹት።
በሩሲያ ተወልዶ ኤምሬትስና ፈረንሳይ ዜግነት የሰጡት ዱሮቭ ባለፈው ወር በፓሪስ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም ቴሌግራም የወንጀለኞች መሰባሰቢያ ሆኗል፤ እጽ የሚያዘዋውሩና የህጻናት ወሲብ ፊልሞችን የሚለቁ ወንጀለኞች ያለምንም ችግር ህገወጥ ድርጊታቸውን ቀጥለዋል የሚሉና ሌሎች ክሶች ቀርቦበት ነበር።
ቢሊየነሩ ዱሮቭ ግን በፈረንሳይ ባለስልጣናት የቀረበበትን ክስ “ሌሎች ለፈጸሙት ወንጀል ልጠየቅ አይገባም” በሚል ክሱን “ግራ የሚያጋባ” ሲል ማጣጣሉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
የዱሮቭ ተቺዎች ግን ቴሌግራም እስከ 200 ሺህ አባላትን የሚይዙ ቡድኖች (ግሩፖች) መፍጠር ማስቻሉ ሀሰተኛ መረጃ፣ የህጻናት ወሲብ ፊልም እና የሽብር ይዘቶች በስፋት እንዲሰራጭ እያደረገ ነው ባይ ናቸው።
እንግሊዝ ባለፈው ወር በተለያዩ ከተሞች ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች የተፈጠረውን ሁከት በማቀጣጠል ሂደት ትልቅ ድርሻ ነበረው ተብሏል።
ዩክሬንም ባለፈው ሳምንት ከሩሲያ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመከላከል በሚል ዜጎች በመንግስት በተመዘገቡ ስልኮች ቴሌግራም እንዳይጠቀሙ አሳስባለች።
የ39 አመቱ ፓቨል ዱሮቭ እስር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ጥሰት ምን ደረጃ እንደደረሰ አመላካች ነው የሚሉ የመብት ተሟጋቾች አሉ።
በተለይ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሌለባቸው ሀገራት ፖለቲከኞች ሃሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹበት የቆዩት ቴሌግራም፥ በጫናም ቢሆን የተጠርጣሪዎችን መረጃ ለሶስተኛ ወገን ለማጋራት ተስማምቷል።
ይህም በርካታ ደንበኞቹን ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑ እየተነገረ ነው።