ዩክሬን የቴሌግራም መተግበሪያ በመንግስት መሳሪያዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል አገደች
የዩክሬን እና የሩሲያ የመንግስት እና የጦር ባለስልጣናት ቴሌግራምን በስፋት ይጠቀሙበታል
ዩኤስአይዲ-ኢንተርኒውስ ባለፈው አመት በሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት 72 በመቶ የሚሆኑ ዩክሬናውያን ዜና ለመከታተል ቴሌግራምን ይጠቀማሉ
ዩክሬን የቴሌግራም መተግበሪያ በመንግስት መሳሪያዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል አገደች።
ዩክሬን መንግስት እና ወታደራዊ ባለስልጣናት የቴሌግራም መተግበሪያን በመንግስት መሳሪያዎች ላይ እንዳይጠቀሙበት እግድ ጥላለች።
የሀገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት እና የመከላከያ ምክር ቤት(አርኤንቢኦ) ይህ ውሳኔ የተላለፈው በ2022 በዩክሬን ላይ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" በከፈተችው ሩሲያ የተቃጣውን ስጋት ለመቀነስ ነው ብሏል።
"ጠላት የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም፣ የኮምፒውተር ቫይረሶችን ለማሰራጨት እና ለሚሳይል ጥቃት ቦታ ለማግኘት በደንብ እየተጠቀመበት ነው"ብሏል ምክር ቤቱ።
የዩክሬን እና የሩሲያ የመንግስት እና የጦር ባለስልጣናት ቴሌግራምን በስፋት ይጠቀሙበታል።
ምክርቤቱ ባወጣው መግለጫ እግዱ የተላለፈው የዩክሬን ከፍተኛ የመረጃ ደህነነት ኃላፊዎች፣ ጦሩ እንዲሁም ህግ አውጭዎች ተሰብስበው ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው።
የዩክሬን ወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖብ የሩሲያ ልዩ ኃይል አገልግሎት የቴሌግራም ተጠቃሚዎች መልእክቱን ቢሰርዙትም፣ የት እንዳሉ ማወቅ እንደሚችሉ የሚያሳይ ተአማኒ መረጃ አቅርቧል።
"የመናገር ነጻነትን ሁሌ እደግፋለሁ፤ መደገፌንም እቀጥላለሁ።ነገርግን የቴሌግራም ጉዳይ የመናገር ነጻነት ጉዳይ አይደለም፤ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው"ብለዋል ቡዳኖቭ።
ቡዳኖቭ እንዳሉት ቴሌግራም መጠቀም የስራቸው አካል የሆኑት ባለስልጣናት ከእግዱ ነጻ ናቸው። የምክርቤቱ የጸረ- የተሳሳተ መረጃ ኃላፊ የሆኑት አንድሪ ኮቫሌንኮ እግዱ ተግባራዊ የሚሆነው በመንግስት መሳሪያዎች ላይ እንጂ በግል ስማርት ሰልኮች ላይ አይደለም ብለዋል።
ኮቫሌንኮ አክለው እንደተናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት እና ወታደራዊ አመራሮች ይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸውን መያዝ እና ማሻሻል ይችላሉ ብለዋል።
ዩኤስአይዲ-ኢንተርኒውስ ባለፈው አመት በሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት 72 በመቶ የሚሆኑ ዩክሬናውያን ዜና ለመከታተል ቴሌግራምን ይጠቀማሉ።
31 ወራትን ያስቆረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።