ቴሌግራም ሩሲያን ጨምሮ ከ30 በላይ ሀገራት መታገዱን ያውቃሉ?
በርካታ ሀገራት ቴሌግራም መንግስታዊ ተቃውሞዎችን ያበረታታል በሚል አግደውታል
የቴሌግራም መስራች የሆኑት ፓቬል ዱራቭ ከሰሞኑ በፈረንሳይ መታሰራቸው ይታወሳል
ቴሌግራም ሩሲያን ጨምሮ ከ30 በላይ ሀገራት መታገዱን ያውቃሉ?
800 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ቴሌግራም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቀባይነቱ እያደገ ይገኛል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት የተመሰረተው ቴሌግራም ከኩባንያዎቹ መስራች አንዱ የሆነው ፓቬል ዱሮቭ በፈረንሳይ ለእስር ተዳርጎ ነበር፡፡
ይህ ሰው ከጥቂት ቀናት እስር በኋላ በዋስ የተፈታ ሲሆን ፈረንሳይን ለቆ እንዳይወጣ የጉዞ እገዳም ተላልፎበታል፡፡
የቴሌግራም መተግበሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቬል ድሮቭ ማን ነው?
በብዙዎች ዘንድ በስልካቸው ላይ በመጫን ተወዳጅ የሆነው ቴሌግራም ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከ31 በላይ ሀገራት እገዳ ተጥሎበታል፡፡
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ እና መስራች ሩሲያዊ መሆኑን ተከትሎ ቴሌግራም የሞስኮ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው በሚል ክስ ሲቀርብበትም ነበር፡፡
ቴሌግራም በፈረንጆቹ 2018 ላይ በሩሲያ እንዳይሰራ እገዳ ተላልፎበት የነበረ ሲሆን ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች ግን ይህን መተግበሪያ በተለያዩ ዘዴዎች መጠቀማቸውን ተከትሎ እገዳው ከሁለት ዓመት በኋላ ሊነሳ ችሏል፡፡
ቻይና፣ ስፔን፣ ዩኬ፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ ዩክሬን፣ ኢራን፣ ሕንድ እና በድምሩ 31 ሀገራት በቴሌግራም ላይ እገዳ ጥለዋል፡፡
ቴሌግራም መተግበሪያ በተለያዩ ሀገራት ተቃውሞዎች እንዲካሄዱ ያበረታታል፣ መረጃዎችን ይደብቃል፣ ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን ያሰራጫል እና ሌሎችም ክሶች ይቀርቡበታል ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
መንግስታትም ቴሌግራም መረጃዎችን ለመንግስት አሳልፎ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ለመተባበር ፈቃደኛ አይደለም በሚል እገዳ ሲያስተላልፉበት ቆይተዋል፡፡
ይሁንና መተግበሪያው በቀላሉ በቪፒኤን እና ሌሎች መንገዶች አማካኝነት መስራት የሚችል ሲሆን በተለይም በርካታ የአውሮፓ ሀገራት እገዳ ጥለውበታል፡፡