ኤምሬትስ በፈረንሳይ የታሰረውን የቴሌግራም መስራች ጉዳይ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለች
የፈረንሳይ መንግስት ለዜጋዋ ፓቨል ዱሮቭ ተገቢውን የማማከር አገልግሎት በአፋጣኝ እንዲሰጠውም በደብዳቤ ጠይቃለች
የቴሌግራም ዋና ቢሮውን በ2017 ወደ ዱባይ ያዛወረው ቢሊየነሩ ፓቨል ዱሮቭ የአረብ ኤምሬትስ ዜግነት ማግኘቱ ይታወሳል
አረብ ኤምሬትስ በፈረንሳይ በቁጥጥር ስር የዋለውን የቴሌግራም መስራች ፓቨል ዱሮቭ ጉዳይ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የፈረንሳይ መንግስት ለቢሊየነሩ ተገቢውን ህጋዊና የማማከር አገልግሎት በፍጥነት እንዲሰጥ ጠይቋል።
“ኤምሬትስ ለዜጎቿ ደህንነት እና ፍላጎት መጠበቅ ቅድሚያ ትሰጣለች” ያለው ሚኒስቴሩ፥ የፈረንሳይ መንግስት ለቴሌግራም መስራቹ ፓቨል ዱሮቭ ድጋፍ እንዲያደርግለት በደብዳቤ መጠየቁን የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም አስነብቧል።
ትውልደ ሩሲያዊው ቢሊየነር ባለፈው ሳምንት ነበር በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አቅራቢያ ከሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው።
ቴሌግራም የሚሰራጩ መረጃዎችን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎችን በበቂ ደረጃ አልቀጠረም፤ የወንጀል ስራዎች እንዳይደረስባቸው እና መከላከል እንዳይቻል የሚያደርግ አሰራርም ዘርግቷል የሚሉ ክሶች በፈረንሳይ በኩል ቀርበውበት ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል።
ታዋቂው የመልዕክት መለዋወጫ ትስስር ገጽ ቴሌግራም ግን መስራቹ እና ዋና ስራ አስፈጻሚው ፓቨል ዱሮቭ የአውሮፓ ህጎችን አክብሮ የሚንቀሳቀስና “ምንም የሚደብቀው ነገር የሌለው” መሆኑን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በሩሲያ የተወለደው ዱሮቭ ከወንድሙ ጋር በመሆን ነበር ቴሌግራምን በፈረንጆቹ 2013 የመሰረተው።
የሩሲያ የስለላ ተቋም ዱሮቭ ቪኮንታክቴ የተባለውን የመጀመሪያ የማህበራዊ ትስስር ገጹን ተጠቃሚዎች መረጃ እንዲሰጥ ያቀረበውን ጥያቄ በወጣቱ ቢሊየነር ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
ዱሮቭ በ2014 ሀገሩን ለቆ ለመውጣት የተገደደ ሲሆን፥ ሩሲያም ከ2018 እስከ 2021 ቴሌግራም ላይ እገዳ ጥላ መቆየቷ ይታወሳል።
የ39 አመቱ ቢሊየነር በ2017 የድርጅቱን ዋና ቢሮ ወደ አረብ ኤምሬትሷ ዱባይ ያዛወረ ሲሆን፥ የኤምሬትስን ዜግነትም አግኝቷል።
በፈረንጆቹ ነሐሴ 2021 የፈረንሳይ ዜግነትንም ያገኘው ፓቨል ዱሮቭ 15 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሃብት እንዳለው የፎርብስ መረጃ ያሳያል።