የማድሪድ ደጋፊዎች ለኪሊያን ምባፔ አቀባበል አደረጉለት
85 ሺህ የሚጠጉ ደጋፊዎች በሳንቲያጎ በርናባው ተገኝተው አዲሱ ፈራሚያቸውን እንደሚቀበሉት ተገምቶ ነበር
የ25 አመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ በማድሪድ ቤት በሚኖረው ቆይታ በአመት 16.2 ሚሊየን ዶላር ይከፈለዋል
ፈረንሳዊው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ ዛሬ እለት በሳንትያጎ በርናባው ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት የመራው ምባፔ በማድሪድ ቤት ለአምስት አመት የሚያቆየውን ስምምነት ፈጽሟል፡፡
ከ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊነት ፈንጠዝያቸው ያልተመለሱት ስፔኖች በዛሬው እለት በማድሪድ ሳንትያጎ በርናባው ተገኝተው ለአዲሱ አጥቂያቸው አቀባበል አድርገዋል።
ምባፔን ለመቀበል የሚገኙ ታዳሚዎች ቁጥር በ2009 ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለመቀበል ተገኝቶ ከነበረው ደጋፊ ቁጥር ሊበልጥ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ከ15 አመታት በፊት ሮናልዶን ለመቀበል በሳንቲያጎ በርናባው 80ሺህ ደጋፊዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን በዛሬው እለት እስከ 85ሺ የሚጠጉ ስፔናውያን ሊገኙ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር፡፡
ምባቤ ከሰአት በኋላ በስታድየሙ ከደጋፊዎቹ ጋር ከሚያደርገው የትውውቅ ፕሮግራም በፊት ከማድሪድ ክለብ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጋር በይፋ የአምስት አመቱን ኮንትራት ይፈራረማል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች የአፍንጫ መሰበር ጉዳት ያጋጠመው ተጨዋቹ በክለቡ ሀኪሞች የሚደረግለትን የህክምና ምርመራ ካጠናቀቀ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
ዛሬ ጠዋት የወጡ የስፔን የስፖርት ጋዜጦች በአሁኑ ወቅት በርካታ ስፔናውያን የእግርኳስ ወዳጆች የኪሊያን ምባቤ ምስል ያረፈበትን 9 ቁጥር ማሊያ ለብሰው በሳንትያጎ በርናባው ስታድየም አካባቢ እንደሚገኙ ዘግበዋል፡፡
የክርስቲያኖ አድናቂ እንደሆነ የሚገልጸው ምባፔ በማድሪድ መጫወት የልጅነት ህልሙ እንደሆነ ይናገራል፡፡
በቡድኑ በሚኖረው ቆይታ ከእንግሊዛዊው አማካይ ጁድ ቤሊንግሀም እና ከብራዚላዊው አጥቂ ቪኒሺየስ ጁኒየር ጋር ይጣመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 15ተኛ የሻምፒውንስ ሊግ ዋንጫቸውን ያነሱት ሎስ ብላንኮዎቹ በጥሩ የአሸናፊነት መነቃቃት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በትላንትናው እለት ለአዲሱ የውድድር ዘመን ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡
ምባቤ ማድሪድ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ በዘንድሮው አመት ከሁለተኛ ዲቪዢዮን ካደገው ሬያል ቫላዶሊድ ጋር በሚያደረገው ጨዋታ ለቡድኑ ግልጋሎቱን መስጠት ይጀምራል፡፡
የ25 አመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ በማድሪድ ቤት ለአምስት አመት የሚያቆየውን ይፋዊ ፊርማ ሲፈራረም በአመት 16.2 ሚሊየን ዶላር የሚከፈለው ሲሆን በተጨማሪም 164 ሚሊየን ዶላር የፊርማ ክፍያ የሚከፈለው ይሆናል፡፡