ምባፔ በፈረንሳይ ምርጫ ዙሪያ የሰጠው አስተያየት ቀኝ ዘመም ፓርቲዎችን አስቆጣ
ስደተኛ ጠል ናቸው የሚባሉት ማሪ ለፔን ምባፔ ብቃት ያለው የእግር ኳስ ተጫዋች ቢሆንም ፈረንሳውያንን ስለምርጫ ማስተማር ግን አይችልም ብለዋል
ፈረንሳይ ዛሬ ምሽት 4 ስአት ካይ ከፖርቹጋል ጋር የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዋን ታደርጋለች
የፈረንሳይ ቀኝ ዘመም ፓርቲው ናሽናል መሪ ማሪ ለፔን ኪሊያን ምባፔ ላይ ትችታቸውን አሰምተዋል።
የ25 አመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ በቅርቡ በተካሄደው የፈረንሳይ አስቸኳይ ምርጫ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ማሸነፋቸውን ተከትሎ የሰጠው አስተያየት ነው ስደተኛ ጠል ናቸው የሚባሉትን ለፔን ያስቆጣው።
ፍራንስ 24 እንዳስነበበው ምባፔ የምርጫውን ውጤት “አስደንጋጭ ነው” ያለ ሲሆን፥ ፈረንሳውያን በቀጣዩ እሁድ በሚደረገው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎችን እንዳይመርጡ ጠይቋል።
ፓሪስ “በቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች እጅ መውደቅ የለባትም” የሚል አስተያየት መስጠቱንም ዘገባው አመላክቷል።
የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ጁሌስ ካውንዴም ፈረንሳውያን ስደተኛ ጠል ቀኝ ዘመም ፓርቲዎችን ከመምረጥ እንዲቆጠቡ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ከሲኤንኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የናሽናል ራሊ ፓሪ መሪዋ ማሪ ለፔን፥ ምባፔ ብቃት ያለው የእግር ኳስ ተጫዋች ቢሆንም ፈረንሳውያንን ስለምርጫ ማስተማር ግን አይችልም ብለዋል።
በፓሪስ የተወለደው ተጫዋች ቤትና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ያልቻሉ በርካታ ስደተኞችን ህመም ሊረዳ አይችልም በሚልም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
“የኪነጥበብ ባለሙያዎችና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች በወር ከ1 ሺህ 300 ዶላር ገደማ ለሚያገኙ ፈረንሳውያን መጻኢ ሊወስኑና ይህን ምረጡ ማለት አይችሉም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፈረንሳውያን የሚበጃቸውን ያውቃሉና እንደ ምባፔ ያሉ ከምርጫው ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ከመስጠት እንዲቆጠቡም ነው ያሳሰቡት።
በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምርጫ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በብዛት ማሸነፋቸው ያሳሰባቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፓርላማውን በትነው አስቸኳይ ምርጫ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በመጀመሪያው ዙር ምርጫባለፉት ሶስት ምርጫዎች ፕሬዝዳንት ለመሆን ተፎካክረው ሳይሳካላቸው የቀረው የማሪ ለፔን ፓርቲ ናሽል ራሊ አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።
ፈረንሳይ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ህዝበ ውሳኔ አደርጋለሁ፤ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ የሚያሰችል ፖሊሲም ተግባራዊ አድርጋለሁ ያሉት ማሪ ለፔን በፈረንሳይ ፖለቲካ ከፊት መሰለፍጥ በተለይ ለስደተኞች ስጋት ይሆናል ተብሏል።
በለፔን ተቃውሞ የተነሳበት ምባፔ ሀገር ፈረንሳይ ዛሬ ምሽት 4 ስአት ላይ በሀምቡርግ ከፖርቹጋል ጋር የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዋን ታደርጋለች።