ድምጻዊ ቴይለር ስዊፍት ከኮንሰርቶች ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ
አሜሪካዊቷ ድምጻዊ በታሪክ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ያጋኘት አርቲስት ተብላለች
ድምጻዊቷ በተያዘው ዓመት በ60 የሙዚቃ ኮንሰርቶች ከአራት ሚሊዮን በላይ ቲኬቶችን ሸጣለች
ድምጻዊ ቴይለር ስዊፍት በአንድ ዓመት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ።
አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቴይለር ስዊፍት በዓለም ሙዚቃ ታሪክ በአንድ ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ከኮንሰርቶች አግኝታለች ተብሏል።
ድምጻዊቷ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ውስጥ በዓለም ላይ 60 የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ማካሄዷ ተገልጿል።
እንደ ኤፒ ዘገባ ድምጻዊቷ ባዘጋጀቻቸው ኮንሰርቶች ላይ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን የኮንሰርት መግቢያ ቲኬቶችን ሸጣለችም ተብሏል።
ከነዚህ ኮንሰርቶች ላይም አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች የተባለ ሲሆን ይህም በአሜሪካ እና በመላው ዓለም በታሪክ የመጀመሪያዋ አድርጓታል።
ከዚህ በተጨማሪም በ2024 ዓመት በተመሳሳይ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኙ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ቲኬታቸው ተሸጦ አልቋልም ተብሏል።
ሌላኛዋ ድምጻዊት ቢዮንሴ በ2023 ገቢ በማግኘት በሁለተኛነት ስትቀመጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአጠቃላይ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከኮንሰርቶች ብቻ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ ተገልጿል።
ድምጻዊት ቴይለር የታየም መጽሄት የ2023 ዓመቱ ቁጥር አንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው በሚል መመረጧ ይታወሳል።
እንዲሁም የዓፕል ሙዚቃ ደግሞ የዓመቱ የሙዚቃ ሰው በሚልም ሌላ ሽልማት የተቀዳጀችው ቴይለር ስፖቲፋይ የተሰኘው የሙዚቃ ማሰራጫ ኩባንያ በአድማጭ ብዛት በአንደኝነት አስቀምጧታል።