ለረጅም ጊዜ በመሳሳም የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈሩት ጥንዶች ተለያዩ
ታይላንዳውያኑ ጥንዶች ከ12 አመት በፊት ነበር ለ58 ስአት ከ35 ደቂቃዎች በመሳሳም ክብረወሰን የያዙት

የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ውድድሩ አደገኛ እና አንዳንድ ህጎቹም ከተሻሻሉ ድንጋጌዎች ጋር የማይጣጣሙ ናቸው በሚል ከ2013 በኋላ እንዳይካሄድ አስቁሞታል
ከ12 አመታት በፊት የአለማቀፍ ትኩረት ስበው የነበሩት ታይላንዳውያን ጥንዶች መለያየታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ኢካቻይ ቲራናራት እና ባለቤቱ ላክሳና በፈረንጆቹ 2013 ለረጅም ስአት በመሳሳም የአለም ክብረወሰንን መስበር ችለው ነበር።
ጥንዶቹ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የእረፍት ህግን ተከትለው ለ58 ስአት ከ35 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ከንፈሮቻቸውን ሳያላቅቁ ቆይተዋል።
ይህም የፍቅራቸውን ጥልቀት እና አካላዊ ብርታታቸውን እንደሚያሳይ ሲዘገብ እንደነበር የህንዱ ኔንዲቲቪ አስታውሷል።
ከሁለት ቀን በላይ ምንም እንቅልፍ ሳይተኙ የመሳሳም ማራቶን ሪከርድን የሰበሩት ጥንዶች የፍቅርና ጽናት ተምሳሌት ሆነው ለ12 አመታት ከዘለቁ በኋላ ግን በፍቺ መለያየታቸው ተሰምቷል።
ኢካቻይ ቲራናራት በማህበራዊ ገጹ ከትዳር አጋሩ ላክሳና ጋር መለያየቱን ገልጿል።
ከላክሳና ጋር ያሳለፍነው አስደናቂ የህይወት ጉዞ ቢቋጭም ክብረወሰን የሰበርንበትንም ሆነ ሌሎች አስደሳች ትዝታዎች አብረውኝ ይዘልቃሉም ብሏል።
የታይላንዳውያን የፍቅር ተምሳሌቶቹ የፍቺ ድግስ አዘጋጅተው በሰላማዊ መንገድ መለያየታቸውንና ልጃቸውም ሲፈልግ ከአባቱ ሲያሻው ከእናቱ ጋር እንዲኖርና በፍቅር ለማሳደግ መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።
ኢካቻይ ከባለቤቱ ጋር የተያዩበትን ምክንያት ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ለረጅም ጊዜ በመሳሳም ለመጀመሪያ ጊዜ የአለም ክብረወሰንን በ2011 የሰበሩት ኢካቻይ እና ላክሳና ከሁለት አመት በኋላ በ2013 የራሳቸውን ክብረወሰን አሻሽለው እስካሁን እንደያዙት ነው።
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ከ2013ቱ ውድድር በኋላ ይህን ዘርፍ ሰርዞታል። በምክንያትነት ያነሳውም የእንቅልፍ ማሳጣትን ጨምሮ ሌሎች የጤና ችግሮችን ያስከትላል፤ በውድድሩ ውስጥ ያሉት ህጎች በቅርብ ጊዜ ከወጡ የተሻሻሉ ድንጋጌዎች ጋር አይጣጣሙም የሚል ነበር።