በአንድ ቀን ስድስት የአለም ድንቃድንቅ ክብረወሰን የሰበረው ህንዳዊ ታዳጊ
"የሰው ካልኩሌተር" የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው የ14 አመት ታዳጊ 100 ባለ አራት ዲጂት ቁጥሮችን በአዕምሮው ለመደመር 30.9 ሰከንዶች ፈጅተውበታል

በቀን ውስጥ ከአምስት እስከ ስድስት ስአት ያለመታከት መለማመዱ ለስኬት እንዳበቃው ይናገራል
ህንዳዊው ታዳጊ አርያን ሹክላ በአንድ ቀን ስድስት የአለም ድንቃድንቅ ክብረወሰኖችን ሰብሯል።
የማሃራሽትራ ነዋሪው የ14 አመት ታዳጊ ሂሳብ ያለምንም አጋዥ መሳሪያ በአዕምሮው በፍጥነት መስራቱ "የሰው ካልኩሌተር" የሚል ቅጽል ስም አሰጥቶታል።
ባለፈው አመት 50 ባለ አምስት ዲጂት ቁጥሮችን በፍጥነት በመደመር የአለም ክብረወሰንን የሰበረው አርያን በቅርቡ በዱባይ በተካሄደ ውድድር በአንድ ቀን ብቻ ስድስት ክብረወሰኖችን መሰባበሩን የህንዱ ኤንዲቲቪ ዘግቧል።
አርያን 100 ባለ አራት ዲጂት ቁጥሮችን ደምሮ ትክክለኛውን ውጤት ለመናገር የፈጀበት 30.9 ሰከንድ ብቻ ነው።
200 ባለ አራት ዲጂት ቁጥሮችን በ1 ደቂቃ ከ9.68 ሰከንድ በመደመርም የአለም ክብረወሰንን ይዟል።
ታዳጊው 50 ባለ አምስት ዲጂት ቁጥሮችን በ18.71 ሰከንድ ብቻ ደምሮ እቅጩን በመናገርም የቀደመውን ክብረወሰን አሻሽሎ ሪከርዱን በእጁ አስገብቷል።
በርካታ ቁጥሮችን በማባዛትና በማካፈልም ፈጣን ስአት አስመዝግቦ በአንድ ቀን ብቻ ስድስት የአለም ድንቃድንቅ ክብረወሰኖችን ይዟል ነው የተባለው።
አርያን የአለማቀፉ የአዕምሮ ሂሳብ ስሌት ማህበር (ጂኤምሲኤ) መስራች አባል ነው።
ከስድስት አመቱ ጀምሮ የሂሳብ ስሌቶችን በፍጥነት በአዕምሮው የሚሰራው አርያን፥ በ2022 በጀርመን በተካሄደ የሂሳብ ስሌት የአለም ዋንጫ ማሸነፉን የማህበሩ ድረገጽ ላይ የወጣ መረጃ ያሳያል።
ባለፉት አመታት በርካታ አለማቀፍ ክብረወሰኖችን የያዘውና ሽልማቶችን የተቀበለው አርያን ከዱባዩ አስደናቂ የውድድር ውጤት በኋላ የስኬትህ ሚስጢር ምንድን ነው? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፥ "በየቀኑ ከአምስት እስከ ስድስት ስአት ያለመታከት መለማመዴ" ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ዮጋ መስራትም እንዲረጋጋ እና በአንድ ነገር ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እንደረጋው ተናግሯል።