3ኛውን ዓይነት የጉበት ቫይረስ በሽታ ለመለየት የተመራመሩ ሳይንቲስቶች የዘንድሮውን የህክምና ኖቤል አሸነፉ
በአሁኑ ወቅት 71 ሚሊዬን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደሚገኙ ይገመታል
ሳይንቲስቶቹ ቫይረሱን ለማከም የሚያስችሉ መላዎችን ዘይደዋልም ተብሏል
3ኛውን ዓይነት የጉበት ቫይረስ በሽታ ለመለየት የተመራመሩ ሳይንቲስቶች የዘንድሮውን የህክምና ኖቤል አሸነፉ
ጉበትን በሚያጠቃው የሄፓታይተስ ቫይረስ ላይ ጥልቅ የምርምር ስራዎችን ሲያደርጉ የነበሩ ሶስት ሳይንቲስቶች የዘንድሮውን የኖቤል የህክምና ዘርፍ ሽልማት አሸነፉ፡፡
ሎሬት ተብለው ሽልማቱን ለማሸነፍ የቻሉት ተመራማሪዎች ሃርቬይ ጄ. አልተር፣ ሚካኤል ሃፍተን እና ቻርለስ ራይስ ናቸው፡፡
ሳይንቲስቶቹ 3ኛውን የቫይረሱን ዓይነት (Hepatitis C virus) በምርምር ከመለየት ባሻገር የበሽታውን መንስዔዎች ለማወቅ ለመመርመር እና ለማከም የሚያስችሉ መላዎችን ለመዘየድም ችለዋል ተብሏል፡፡
ዛሬ ጉባዔውን ስዊድን በሚገኘው የካሮሊንስካ የህክምና ተቋም ያደረገው የዓለም አቀፉ የሽልማት ተቋምም ይህንኑ አበርክቷቸውን ታሳቢ በማድረግ “ሎሬት” ሲል ሸልሟቸዋል፡፡
የተመራማሪዎቹ ግኝት ዓለም አቀፍ የጤና ችግር በመሆን ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገውን ቫይረስ ለማከም ወሳኝ እንደሆነም ተቋሙ ገልጿል፡፡
ይህ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ነው የተባለም ሲሆን ከቫይረሱ ሊፈውስ እንደሚችልም ተስፋ ተሰንቋል፡፡
ተመራማሪዎቹ የበሽታውን መንስዔዎች በመለየት የደም ናሙናዎችን መመርመርን ጭምር ቀላል አድርገውታል፡፡
ቫይረሱ ጉበትን በማጥቃት ለካንሰር ጭምር የሚያጋልጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 71 ሚሊዬን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ምርምሩ እኚህን ጨምሮ ሌሎች ሚሊዮኖችን ሊታደግ እንደሚችልም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ዛሬ የጀመረው ጉባዔ እስከመጪው ሰኞ የሚዘልቅ ነው፡፡
የፊዚክስ፣የኬሚስትሪ፣የስነ ጽሁፍ፣የሰላም እና የምጣኔ ሃብት ሎሬቶች በጉባዔው የየዕለት ውሎዎች የሚመረጡም ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የባለፈው ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡