መሪጌታ በላይ "እምቦጭ ያጠፋል"ያሉት መድኃኒት ውጤታማ አይደለም ተባለ
"ያገኘሁት መድሃት እምቦጭን ሙሉ በሙሉ ያጠፋል፤ ለምን አሁኑኑ አንሞክረውም"ብለዋል መርጌታ በላይ አዳሙ
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲና የምርምር ተቋማቶች ያዋቀሩት ኮሚቴ መድሃኒቱ “ውጤታማ” ስላልሆነ ህብረተሰቡ አረሙን ለማጥፋት ይዘጋጅ ብሏል
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲና የምርምር ተቋማቶች ያዋቀሩት ኮሚቴ መድሃኒቱ “ውጤታማ” ስላልሆነ ህብረተሰቡ አረሙን ለማጥፋት ይዘጋጅ ብሏል
መርጌታ በላይ አዳሙ የእምቦጭ አረም ማጥፊያ መድሃት ማዘጋጀታቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ያዘጋጁት መድሃኒትም እምቦጭን እንደሚያጠፋ ገልጸው የነበረ ሲሆን አስፈላጊው ሙከራ እንደተካሄደበትና ዕውቅናም እንደተሰጣቸው ገልጸው ነበር፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ እና የተለያዩ የምርምር ተቋማት ቴክኒካል ኮሚቴ አዋቅረው የመርጌታ በላይ አዳሙን ሥራ ሲከታተሉ ቆይተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሕብረተሰቡ መርጌታ በላይ አዳሙ ከጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት የሚረዳ መድኃኒት አለኝ የሚሉት መድኃኒት ውጤታማ አለመሆኑን ህዝቡ ተገንዝቦ አረሙን ለመጥፋት እንዲዘጋጅ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ለአብመድ እንደገለጹት "መርጌታ በላይ አዳሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙከራ የሠሩት የእምቦጭ አረም ማጥፊያ መድኃኒት በአነስተኛ ደረጃ አረሙን ማጥፋት ቢቻልም የጎንዮሽ ጉዳቱ በሳይንስናዊ ምርም አልተረጋገጠም"ብለዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ“የላብራቶሪ ሥራ ለመሥራትም መርጌታው ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል” አለመስጠታቸውን ለአብመድ አብራርተዋል፡፡
የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ"የመርጌታ በላይ ጉዳይ ኅብረተሰብ ወደ ቀልቡ ተመልሶ ጣናን ከእምቦጭ እንዳይከላከል እያደረገ ነው" ብለዋል። በ2013ዓ.ም በሕብረተሰቡ ጉልበት እና በማሽን ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚደረገውን ጉዞም እያደናቀፈ እንደሚገኝ የገለጹ ዶ/ር አያሌው "በአሉቧልታ ጊዜያችን ባይጠፋ መልካም ነው" ሲሉ የመሪጌታን በላይ ሥራ ውጤታማ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
መግለጫውን በተመለከተ አል ዐይን ኒውስ እምቦጭን የሚያጠፋ መድሃኒት አግኝቻለሁ ያሉትን መሪጌታ በላይ አዳሙን አነጋግሯል፡፡ እርሳቸውም በአነስተኛ ደረጃ ያጠፋል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ገልጸው፤ የተሰጠው መግለጫ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በተሰጠው መግለጫ እንደማይስማሙ ያነሱት መሪጌታው መግለጫው ሲሰጥ ሊጠሩ ይገባ እንደነበርም ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ዓሳ ምርምር ማዕከል በኮሚቴነት የሰሩት አቶ አዳነ መላኩ የመርጌታ ሥራ ሳይንሳዊ መንገዱን ተከትሎ የተሠራ ባይሆንም ዓረሙን በመጠነኛ ደረጃ ማጥፋቱን ተናግረው ነገር ግን በውስጡ የሚገኙ ትንንሽ ነፍሳትን እንደሚገድልም ገልጸዋል። መድሃቱ ዓሳ ላይ ችግር ባያደርስም ሰዎች ሲመገቡት ሊኖር የሚችለው ተፅዕኖ አልታየም ሲሉ አቶ አዳነ ቢያነሱም መሪጌታ በላይ ግን ዓሳ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ ገልጸው ለምን አሁኑኑ አመንሞክረውም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
መድኃኒቱ ከዕፅዋት ብቻ የተቀመመና በብዝኃ ሕይወት ላይም ጉዳት የማያደርስ መሆኑን የገለጹት መሪጌታ በላይ በቀጣይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎችና ሌሎችም በተገኙበት በሳይንሳዊ መንገድ ተፈትሾ ውጤቱ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉም መርጌታ በላይ ተናግረዋል፡፡
ገለልተኛ አካላት ባሉበት በሕዘብ ፊት እንዲሞከርና የተግባር ሥራ እንዲታይ እፈልጋለሁ ሲሉ መሪጌታ በላይ ገልጸዋል፡፡ይህንን መድሃኒት ለማግኘት ሰባት ዓመት የፈጀ ምርምር ማድረጋቸውን ያነሱት መሪጌታው አስፈላጊ የሚባ ዕውቅናዎችና ሰነዶች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡