የምክር ቤቱ አባል ሀገራት በኢራን የኑክሌር ጉዳይ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው
41ኛው የገልፍ ትብብር መደበኛ ጉባዔ በሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ሰብሳቢነት፣ በዓለም ትልቁ በሆነው እና ለኮንሰርት በተዘጋጀው በሳዑዲ አል ኡላ በሚገኘው የመስታወት አዳራሽ በመካሔድ ላይ ነው፡፡
በጉባዔው በርካታ ጉዳዮች እንደሚዳሰሱ የሚጠበቅ ሲሆን ከነዚህም መካከል ቀጣናዊ እና ስትራቴጂካዊ ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉዳዮች ፣ የኢራን የኑክሌር ጉዳይ እና የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ጉዳይ ይገኙበታል፡፡
የኳታሩን አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒን ጨምሮ ፣ ለጉባዔው ሳዑዲ አል ኡላ የተገኙ የገልፍ ሀገራት መሪዎች እና ልዑካንን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሀመድ ቢን ሳልማን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ልዑል አልጋ ወራሹ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የገልፍ ትብብር ም/ቤት ሀገሮቻችንን በሚያስተሳስሩ ልዩ ግንኙነቶች ላይ ተመስርቶ የተቋቋመ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣናው ያለውን አቅም በማሰባሰብ ከኢራን የተጋረጠብንን ፈተና መጋፈጥ አለብን፡፡ የኢራን የኑክሌር እና ባለስቲክ ሚሳይል ፕሮግራም ዋነኛ ፈተናችን ነው ሲሉም የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ተናግረዋል፡፡
የኩዌት ኤሚር ሼክ ናዋፍ አል አህመድ አል ጃቢር በበኩላቸው የገልፍ ሀገራት ለቀጣናው ህዝብ የሚያደርጓቸውን የጋራ ጥረቶች አድንቀዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ሳዑዲ ለጉባዔው ዝግጅት ላደረገችው የተቀናጀ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ጉባዔው በመስታዋት በተሰራ አዳራሽ ውስጥ መካሄዱ ታሪካዊ እንደሚያደርገውም ነው የገለጹት፡፡
500 መቀመጫ ያለው ባለመስታወት አዳራሽ ትልቁ የመስታወት አዳራሽ በሚል በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ጊነስ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሯል፡፡
የገልፍ ሀገራት መሪዎች የአል ኡላ ጉባዔ ሰነድ ላይም ፈርመዋል፡፡