ከ84 አመታት በፊት በ3 ቀናት ውስጥ ከ30ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የፋሺስት ጣሊያን ሰለባ ሆነዋል
በ1888 አድዋ ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት የፋሺስት ጣሊያንን ጦር በማሸነፍ ድል ማድረጉን ተከትሎ ፣ ፋሺስት ጣሊያን የሽንፈት ካባ ተከናንባ የኢትዮጵያን ምድር ለቃ ወጣች፡፡
ነገር ግን በአድዋ ሽንፈት ቂም የያዘችው ጣሊያን ከ35 ዓመታት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን በመውረር ብዙ አትዮጰያዉያንን በግፍ ለሞት ዳርጋለች፡፡
ጊዜው የዓለም መንግስታት ማህበር (League of Nations) የተመሰረተበትነበር፤ ኢትዮጵያ ለዚሁ ማህበር ወረራው ተገቢ አይደለም ብላ አቤት ብትልም አጋርነት ካሳዩ ጥቂት ሀገራት ውጭ ሰሚ አላገኘችም፡፡
ይሁንና የዓለም መንግስታት ማህበር ከተመሰረተ ከአምስት ዓመታት በኋላ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ጀመረች፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስትና አርበኞች ሀገርን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡
ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ የጣሊያንን ድርጊት አዲስ ለተቋቋመው የመንግስታት ማህበር ለማልከት ወደ ውጭ ሃገራት ቢሄዱም ህግና ሉዓላዊነት በወቅቱ ትኩረት ሊሰጣቸው ስላልቻለ ኢትዮጵያውያ በብቸኝነት የነጻነት ተጋድሏቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡
ንጉሰ ነገስቱም በብሪታኒያ እንዲቆዩ ሆነ፡፡ ጣሊያን በአድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስና ኢትዮጵያን ለመውረር ባደረገው ወረራ የተበሳጩት ኢትዮጵያውያኑ አርበኞች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ፣ ከ84 ዓመታት በፊት (የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም) በኢትዮጵያ የፋሺስት ጣሊያን አስተዳደር ተወካይ (ኃላፊ) የነበረውን ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒን ለመግደል ሙከራ አደረጉ፡፡ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የወረወሯቸው ቦምቦች ግራዚያኒን ጨምሮ ሌሎች በስፍራው የነበሩ ሹማምንትን አቆሰሉ፡፡
በዚህም የባሰ ለግዲያ የሚያነሳሳ ምክንያት በማግኘት ፋሺስቶች የበቀል ሰይፋቸውን በኢትዮጵያውያን ላይ መዘዙ፡፡ በሦስት ቀናት ውስጥም ከ30ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የፋሺስቶች ሰለባ መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል፡፡
የበቀል እርምጃው ከአዲስ አበባ አልፎ ደብረ ሊባስ ገዳምም በመድረስ ቀሳውስትና ምዕመናን መገደላቸውንም ታሪክ መዝግቦታል፡፡
ከዚያን ግዜ ጀምሮ የካቲት 12 በኢትዮጵያውያን ዘንድ በየዓመቱ ይከበራል፡፡ የመታሰቢያው ስነስርዓት በተለይም በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት ስር ነው የሚካሔደው፡፡
በዛሬው የየካቲት 12 ሰማዕታት 84ኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስድስት ኪሎ የመታሰቢያ ሀውልት በመገኘት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
በተጨማሪም የአባት አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን በሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ላይ አርበኞች እና የተለያዩ ሰዎች ተገኝተዋል።