በማይካድራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የእርሻ ካምፕ ውስጥ የሕወሓት የጦር መሳሪያዎችና ማሰልጠኛ ተገኘ
የተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ ልብሶች፣ የአልሸባብ እና የኦነግ ሸኔ ወታደራዊ ልብሶችም መገኘታቸው ተገልጿል
የተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ ልብሶች፣ የአልሸባብ እና የኦነግ ሸኔ ወታደራዊ ልብሶችም መገኘታቸው ተገልጿል
በማይካድራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የእርሻ ካምፕ ውስጥ የሕወሓት የጦር መሳሪያዎችና ማሰልጠኛ ተገኘ
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ከማይካድራ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኝ የእርሻ ካምፕ ውስጥ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ ከአንድ ሺህ በላይ የተለያዩ ፈንጂዎች ተገኝተዋል። የእርሻ ካምፑ የትህነግ (ሕወሓት) ቡድን አመራሮች ሲጠቀሙበት የቆየ መሆኑን አብመድ ዘግቧል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ የቴዎድሮስ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ሎጀስቲክ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዘመድ ግርማው እንደገለፁት በካምፑ የራዲዮ መገናኛዎች፣ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ ልብሶች፣ የአልሸባብ እና የኦነግ ሸኔ ወታደራዊ ልብሶች፣ የሠው ማሠቃያ ሠንሰለቶች፣ መፅሐፎች፣ ካሴቶች፣ ሲዲዎች እና የተለያዩ ፈንጆች ተገኝተዋል።
በአንድ መጋዘን ውስጥ ከተገኙት ፈንጂዎች መካከል 700 ፀረ ሰው ፣ 200 ፀረ ታንክ ፣ 200 ሳሙና መሠል ፈንጂ እና ከ100 በላይ ፀረ ፎቅ ወይም ፀረ ድልድይ ፈንጅዎች ተገኝተዋል።
ስፍራው ለማሰልጠኛነትም ያገለግል እንደነበር ዘገባው ያመለክታል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ጥቃት መፈጸሙ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መቀሌን መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡ ሠራዊቱ መቐሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሠራዊቱ ንብረት የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ የሕወሓት የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠሩን ገልጿል፡፡
የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻው መጠናቀቁን የገለጸው የፌዴራል መንግሥት በቀጣይነት በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን እና ከመከላከያ ሠራዊት የከዱ አመራሮችን የማደን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በወንጀል የሚፈለጉ አመራሮች ይገኙበታል የተባለው ስፍራ በመከላከያ ሠራዊት ተከቦ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡