በማይካድራ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 700 እንደሚደርስ ተገለጸ
በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ምርኮኞች ሰብኣዊ አያያዝ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተጠቁሟል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በማይካድራ የተጨፈጨፉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልጿል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ዳንሻ፣ ሁመራና ማይካድራ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ ማድረጉን ገልጾ፣ በአከባቢው “በጁንታው” የሕወሓት ቡድን የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አብራርቷል፡፡
"የጁንታው ቡድን" በሁመራና በማይካድራ ከተሞች የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ትኩረት በማድረግ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማድረጉን ቦርዱ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
በተለይ በማይካድራ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 700 እንደሚደርስ ፣ ነገር ግን በየጫካው እስካሁን ያልተገኙ አስከሬኖች ሊኖሩ እንደሚችሉና በዚህም የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ ጠቁመዋል፡፡
"ሳምሪ" የተባለው የወጣቶች ቡድን ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ቢፈጽምም ፣ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ገዳዩ ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች በመደበቅ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲተርፍ ማድረጋቸውን መርማሪ ቦርዱ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በዳንሻ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦችን በማፈን እንግልት እንደተፈጸመባቸውም ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡
"ከሃዲው ቡድን" ለጥፋት ያሰለፋቸውና በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉ የትግራይ ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት
ሰብኣዊ አያያዝ እየተደረገላቸው መሆኑንም መርማሪ ቦርዱ አስረድቷል፡፡
ቦርዱ ጉብኝቱን የጀመረባቸው የባህርዳርና የጎንደር የሲቪል አየር ማረፍያዎች ላይ የደረሰው ጉዳት አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በከተሞቹ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለመከላከያ ሰራዊትም ሆነ "ከሃዲው ቡድን" ለጥፋት አሰልፏቸው ለቆሰሉ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ተመሳሳይ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም የጎንደር ከተማ ማህበረሰብና የከተማ መስተዳድሩ ታካሚዎቹን በመንከባከባቸው፤ እንዲሁም ከሀዲው የህወሃት ቡድን ባደረሰባቸው ጥቃት ከትግራይ ክልል በመሰደድ በከተማዋ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ሰብኣዊ ድጋፍ ስለማድረጋቸው አመስግነዋል፡፡
መሪማሪ ቦርዱ በቀጣይነት በመንግስት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ወንጀለኞቹን የማደኑ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሱዳን ድንበር አከባቢ ሌላ አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲደረግ በማለት አሳስቧል፡፡
በህክምና ላይ ከሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የባንክ ደብተርና ሌሎች ማስረጃዎች የጠፋባቸው ስለሚገኙ መፍትሄ እንዲሰጥ፣ የተበታተኑ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦች እንዲገናኙ ቢመቻች እንዲሁም የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ያለውን በጀት ለተፈጠረው ድንገተኛ አደጋ አሟጦ በመጠቀሙ ድጎማ ቢደረግለት የሚሉ ምክረ ሃሳቦች በመርማሪ ቦርዱ ተሰጥቷል፡፡
መርማሪ ቦርዱ በቀጣይ ወደ ራያ፣ አላማጣ፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ መቀሌና በሌሎች አከባቢዎች ተገኝቶ የምርመራ ስራውን እንደሚያከናውን የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል፡፡
ዘገባውን ያገኘነው ከሕ/ተ/ም/ቤት የፌስቡክ ገጽ ነው፡፡