የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ከወጣ በኋላ ታሊባን ድል እየቀናው መሆኑን ገልጿል
የአፍጋኒስታኑ ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ በዝርዝር ይፋ ያልተደረገ የጸጥታ ዕድቅ ይፋ ማድረጋቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ይህ የጸጥታ ዕቅድ የታሊባንን ጥቃት ለመመከት እንደሆነ ቢገለጽም ጉዳዩ ግን በዝርዝር አለመቅረቡ ነው የተነገረው። በሀገሪቱ መንግስት እና በታሊባን ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተባለ ውጊያ እየተደረገ መሆኑን ተከትሎ የአፍጋኒስታን ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንደገጠማቸው እየተገለጸ ነው።
በአፈጋኒስታን ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ያለው የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና የአሜሪካ ጦር ከ 20 ዓመታት በኋላ መውጣታቸውን ተከትሎ መሆኑም ተገልጿል።
ታሊባን በሀገሪቱ የግዛቶችን ከተሞችን ለመቆጣጠር ጥረት ላይ ነው ቢባልም አሜሪካ ግን በታሊባን ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ሲኤንኤን ዘግቧል።
አሜሪካ እና ብሪታኒያ ታሊባንን በጦር ወንጀል መጠየቅ እንዳለበት እየገለጹ ናቸው፡፡ በአፍጋኒስታን የብሪታኒያ ኤምባሲ ካንዳሃር በሚባለው አካባቢ በርካታ ዜጎች በታሊባን መጨፍጨፋቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
ይህ ጭፍጨፋም በጦር ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ገልጾ መጣራት እና የታሊባን ኮማንደሮች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።
ታሊባን የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ከስልጣን ካልተነሱ ሰላም እንደማይረጋገጥ ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል።
የአሜሪካ እና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከአፍጋኒስታን ለቆ መውጣት ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ ታሊባን የአፍጋኒስታንን በርካታ ግዛቶች መቆጣጠሩን እየገለጸ ነው።