አሜሪካ ከ13 ዓመታት በኋላ ጦሯን ከኢራቅ እንደምታስወጣ ገለጸች
በኢራቅ ያለው የአሜሪካ ጦር በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ኢራቅን ለቆ ይወጣል ተብሏል
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2011 ዓመት ጦሯን ከኢራቅ አውጥታ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ልካ ነበር
የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እንዳሉት በኢራቅ ያለው የአሜሪካ ጦር በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ኢራቅን ለቆ ይወጣል ብለዋል።
ፕሬዘዳንት ባይደን ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ከኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲኒ ጋር በነጩ ቤተመንግስት ከተወያዩ በኋላ ነው።ይሁንና ኢራቅ ከአሸባሪው አይ ኤስ ኤይ ኤስ ጋር ለምታደርገው ውጊያ ስልጠናዎችን እና ተጨማሪ ድጋፎች መስጠቷን እንደምትቀጥል ፕሬዘዳንቱ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ ኮማንደር ቃሲም ሱለማኒ ከአንድ ዓመት በፊት በባግዳድ በአሜሪካ ድሮን መገደሉን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ኢራንን ይልቀቅ የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት ሲነሱ ቆይተዋል።
የኢራቅ ፖለቲከኞችም ሀገራቸው የአሜሪካ እና ኢራን የጦር ውጊያ ሜዳ ልትሆን እንችላለን የሚሉ ስጋቶችን ሲያነሱ የቆዩ ሲሆን በኢራን የሚደገፉ የሀገሪቱ ፖለቲከኞችም በግልጽ የአሜሪካ ጦር እንዲለቅ ሲወተውቱም ነበር።
አሜሪካ ኢራቅን እንድትለቅ በግልጽ በተለያዩ አካላት ከመጠየቋ ባለፈ የሱኒ እስላማዊ አክራሪ ቡድን የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን በሮኬት አጥቅተዋል።
አሜሪካ ወደ ኢራቅ ጦሯን የላከችው የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዘዳንት ጅምላ ጨራሽ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አለው በሚል ነበር በፕሬዘዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን ነበር።
በፈረንጆቹ 2003 ዓመት ወደ ኢራቅ ጦሯን የላከችው አሜሪካ የተባለው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባይገኝም ፕሬዘዳንት ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ተነስተው በስቅላት መቀጣታቸው ይታወሳል። ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ባግዳድ ያመራው የአሜሪካ እና አጋሮቿ ጦር ከ13 ዓመታት በኋላ ኢራቅን ለቆ እንደሚወጣ ተገልጿል።
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲኒ በበኩላቸው ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል።ሁለቱ ሀገራት አሁን ላይ በኢኮኖሚ፤በጤና፤በአካባቢ ጥበቃ እና ትምህርት ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢራቅ የውጭ ሀገራት ጦር አያስፈልጋትም ብለዋል።
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2011 ዓመት ጦሯን ከኢራቅ አስወጥታ የነበረ ቢሆንም በባግዳድ የሽብርተኛው አይ አይ ቡድን ጥቃት ማየሉን ተከትሎ የኢራቅ መንግስት በድጋሚ ባቀረበው ጥያቄ ሊመለስ ችሏል።