ወታደሮቹ የባይደን በዓለ ሲመት ከመፈጸሙ 5 ቀናት በፊት ሶማሊያን ለቀው ይወጣሉ ተብሏል
አሜሪካ በሶማሊያ የሚገኙ ወታደሮቿን ልታስወጣ ነው
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሶማሊያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ሊያስወጡ መሆኑ ሶማሊያውያንን ቅር አሰኝቷል ተባለ፡፡
ሶማሊያውያኑ ስኬታማ ጸረ አልሸባብ ዘመቻዎች በመደረግ ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት ይህ መባሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ወታደሮች በሶማሊያ ወታደሮች ስልጠና እና የዘመቻ ውጤታማነት የጎላ አበርክቶ አላቸው ሲሉ ለሮይተርስ የገለጹት የሃገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አዩብ እስማኤል ዩሱፍ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የትራምፕን ውሳኔ እንዲሽሩ ጠይቀዋል፡፡
የፕሬዝዳንት አብዱላሂ ሞሃመድ ፋርማጆ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡
ወታደሮቹ በሶማሊያ እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አልሸባብን መሰል ሽብርተኞችን ለመደምሰስ በሚደረጉ የጸረ ሽብር ተግባራት እና ዘመቻዎች በስልጠና እና በሌሎችም መንገዶች ሲሳተፉ ነበር፡፡
ሆኖም የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን ትናንት ባደረገው የኦንላይን ስብሰባ አዲስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ውሳኔው በሶማሊያ የሚገኙ 700 ገደማ ወታደሮች በአዲሱ የፈረንጆች አመት የመጀመሪያ 15 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ የሚል ነው፡፡
ይህ ጆ ባይደን የፕሬዝዳንትነት በዓለ ሲመታቸው ተፈጽሞ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከመግባታቸው 5 ቀናት በፊት የሚሆን ነው እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፡፡
ውሳኔው ትራምፕ ነጩን ቤተ መንግስት ከመልቀቃቸው በፊት ለማስፈጸም ካቀዷቸው የቤት ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ የሚገኙ የሃገሪቱ ወታደሮች እንደሚወጡ መነገሩም አይዘነጋም፡፡