አገር አቀፍ ክርክሩ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ የሚካሄድ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር የማከናወን ፍላጎት ላላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሚዲያዎች ጥሪ አቀረበ፡፡
ከአሁን ቀደም የተወሰኑ ተቋማት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የገለጸው ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርን ለማስተባበር እንደሚፈልግ አስታውቋል።
በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥያቄ ያቀረቡም ሆኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ የመስራት ፍላጎት ያላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሚዲያዎች በተናጠል ወይም በጋራ ያላቸውን ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በግንባር ወይም በኢ-ሜይል አድራሻ (media@nebe.org.et) እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
መግለጫው ተቋማቱ ሊያዘጋጁ የሚፈልጉትን ክርክር ዓላማ፣ የማከናወኛና የሚቀርብበት መንገድ፣ የስነ ምግባር ኮድ እና ሌሎችንም ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች እንዲያካትትም ነው ቦርዱ የጠየቀው፡፡
ሆኖም ክርክሩን ከማመቻቸት ባለፈ ለዝግጅቱ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ እንደማያደርግ አስታውቋል።
የካቲት 8 2013 ዓ/ም የተጀመረው የእጩዎች ምዝገባ በቦርዱ የምርጫ ሰሌዳ መሰረት ነገ እሁድ የካቲት 21 የሚጠናቀቅ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡