ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የዕጩዎች ምዝገባ ቀንን ይፋ አደረገ
በ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ለመወዳደር የሚፈልጉ እጩዎችን ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለመመዝገብ የሚያስችል የጊዜ ሰሌዳ መዘጋጀቱ የሚታወስ ነው
ቦርዱ ኦሮሚያን ጨምሮ የአራት ክልሎችን የዕጩዎች ምዝገባ ቀንንም ይፋ አድርጓል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች የዕጩዎች ምዝገባ ቀንን ይፋ አደረገ፡፡
ቦርዱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ እና በሃረሪ ክልላዊ መንግስታት የሚወዳደሩ እጩዎች የሚመዘገቡበትን ቀንም ይፋ አድርጓል፡፡
በመሆኑም በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እና ቀደም ሲል በተጠቀሱት ክልሎች የሚገኙ እጩዎች ምዝገባ ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 11፡30 እንደሚከናወን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በእጩነት የሚመዘገቡት በቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ በግል ወይም በፖለቲካ ድርጅት አባልነት ለመወዳደር የሚፈልጉ ናቸው፡፡
በአካል ቀርቦ መመዝገብም ይጠበቅባቸዋል፡፡
በፖለቲካ ድርጅት ተወክለው የሚቀርቡ እጩዎች በፓርቲው መወከላቸውን እና በእጩነት ለመቅረብ መስማማታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ከእጩነት ማመልከቻ ቅጽ እና ከሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች ጋር አያይዘው በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል መመዝገብ እንደሚችሉ ነው ቦርዱ ያስታወቀው።
አንድ እጩ በአንድ ጊዜ መወዳደር የሚችለው/የምትችለው በአንድ የምርጫ ክልል እና ለአንድ ምርጫ አይነት ብቻ ነውም ብሏል ቦርዱ።
በእጩነት ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ያስቀመጠው ቦርዱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወነው በየምርጫ ክልሎቹ እንደሆነም ይፋ አድርጓል፡፡
ዕጩ ሆኖ ለመመዝገብ ለፌዴራል እና ለክልል ምክር ቤቶች በግል የሚወዳደሩ ዕጩዎች 2 ሺ 500፤ አካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ደግሞ 1 ሺ 500 የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እጩ ሆነው መቅረብ የሚፈልጉ ደግሞ ለዚህኛው ጠቅላላ ምርጫ ብቻ በሚል በተወካዮች ምክር ቤት በተወሰነው መሰረት የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም።
ቦርዱ የተቀሩትን ክልሎች የእጩዎች ምዝገባ ሰሌዳ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ እና የደቡብ ምዕራብ ህዝበ ውሳኔ ተዳብለው ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም ይካሄዳሉ መባሉ የሚታወስ ነው፡፡