ሀገራዊ ምርጫው እና የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ግንቦት 28 እንዲደረጉ ሀሳብ ቀረበ
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 5 ቀን ይሆናል
የጊዜ ሰሌዳው የትግራይ ክልልን እንደማይመለከት ተገልጿል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን እንዲሆን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አቀረቡ፡፡
የጊዜ ሰሌዳውን በተመለከተም ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአዲስ አበባ በመወያየት ላይ ነው፡፡
በውይይቱ በ2013 ዓ/ም የሚደረገው ሃገር አቀፍ ምርጫ አጠቃላይ የትግበራ መርሃ ግብር ቀርቧል፡፡
በቀረበው የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 16 2013 ዓ.ም ድረስ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን መክፈት፣ ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እና የመራጮች ምዝገባ ይካሄዳል፡፡
ከጥር 22 እስከ የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ/ም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት ማስገቢያና መወሰኛ፣ የካቲት 8 እስከ የካቲት 21 የዕጩዎች ምዝገባ እንዲሆን ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
ቦርዱ ሌሎች ዝርዝሮችንም ያካተተ የምርጫ ማስፈጸሚያ መርሃ ግብርንም ነው ይፋ ያደረገው፡፡
የምርጫ ሰሌዳው የትግራይ ክልልን አይመለከትም ተብሏል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከቦርዱ ጋር በትብብር መስራት በሚችልበትና በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ አዋጅ ለምርጫ በሚስማማ መልኩ መመቻቸቱ ሲረጋገጥ በክልሉ የሚደረገውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ቦርዱ እንደሚያሳውቅ አስታውቋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀንም ዋናው ምርጫ በሚደረግበት ዕለት ግንቦት 28 ቀን 2013 እንዲሆን ቦርዱ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ድምጽ መስጫ ቀን ደግሞ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሆን ነው ቦርዱ ሀሳብ ያቀረበው፡፡
የምርጫው ውጤትን በተመለከተ ለሀገር አቀፍ ምርጫ በምርጫ ጣቢያ ውጤት የሚገለጽበት ቀን ከግንቦት 28 እስከ 29 ቀን 2013 ሲሆን በምርጫ ክልል ደረጃ ደግሞ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 3 ቢሆን ተብሏል፡፡
ለአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ሰኔ 5 እስከ ሰኔ 6፤ በምርጫ ክልል ደረጃ ደግሞ ሰኔ 6 እስከ ሰኔ 11 ቀን 2013 እንዲሆን ሀሳብ ቀርቧል፡፡
የመጨረሻው ውጤት በቦርዱ ይፋ የሚሆንበት ቀን ደግሞ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 21 ይሆናል ነው የተባለው፡፡