የአሜሪካ ዶላር በዓለም ንግድ ላይ ያለው ድርሻ ከ20 ዓመት በኋላ ቅናሽ አሳይቷል
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት 90 በመቶ የዓለማችን የውጭ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በአሜሪካ ዶላር መከናወኑን ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም አይኤምኤፍ ገልጿል፡፡
በዓለማችን ከተካሄደው አጠቃላይ ንግድ ውስጥ ከ6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ በአሜሪካ ዶላር የተካሄደ ሲሆን ይህም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ሆኖ መመዝገቡን አይኤምኤፍ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ዶላር ለምን ይሄን ያህል ቅናሽ አሳየ? የሚለው ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ሮይተርስ ኢኮኖሚስቶችን እና የቢዝነስ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ሰፊ ሀተታ ጽፏል፡፡
ባለሙያዎቹ እንዳሉት ከሆነ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ማምራቷን ተከትሎ አሜሪካ 640 ቢሊዮን ዶላር መጠን ያለው የሩሲያ መጠባበቂያ ወርቅን መያዟ ዋነ ኛው ምክንያት ነው፡፡
በርካታ የአለማችን ሀገራት የውጭ መጠባበቂያ እና የንግድ ግንኙነታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳለጥ በሚል ወርቅ ያከማቻሉ፡፡
ሩሲያም ይህ ለዓለም ንግድ በሚል ያስቀመጠችውን የመጠባበቂያ ዶላር በአሜሪካ መያዙ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ያላቸውን የውጭ መጠባባቂያ ሀብት በዶላር ብቻ ማከማቸት ስህተት መሆኑን መረዳታቸው ለዶላር መቀነስ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቅሰዋል፡፡
አሜሪካ በሩሲያ ላይ የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎ የዓለማችን ሀብታም የሚባሉ ሀገራት የውጭ መጠባበቂያ ሀብታቸውን ወደ ተለያዩ ገንዘቦች በመቀየር ላይ ናቸውም ተብሏል፡፡
ለአብነትም በአሜሪካ ከፍተኛ መጠባበቂያ ሀብት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ቱርክ እና ሌሎችም ሀገራት መጠባበቂያ ሀብታቸው በአሜሪካ ዶላር ላይ ብቻ እንዳይመሰረት አድርገዋል ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም የአሜሪካ ዶላር በዓለም ንግድ ግብይት ላይ ያለው ድርሻ እንዲቀንስ ማድረጉን የሚናገሩት ባለሙያዎቹ የዶላር ጸፅዕኖ እየቀነሰ መሄዱ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና የአሜሪካ ዶላር የዓለም ዋነኛ የንግድ መገበያያ ገንዘብ ሆኖ ይቀጥላል የተባለ ሲሆን በርካታ የዓለማችን ሀገራት የዓለም ንግድ በጥቂት ሀገራት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ አለመፈለጋቸው የዶላርን የበላይነት እያዳከመው እንደሚሄድ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ የዶላር የበላይነትን መቆጣጠሯ ሀገራት የዋሸንግተን ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነት እንዳይመሰርቱ ማድረጉ ለዶላር ፍላጎት መቀነስ ሌላኛው ምክንያት ነውም ተብሏል፡፡
የቻይናው ዩዋን፣ የሩሲያ ሩብል፣ የሕንዱ ሩጲ እና የአረብ ኢምሬት ድርሃም በ2022 ዓመት የዶላርን የዓለም ንግድ ድርሻ ከተጋሩ መገበያያዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በርካታ የዓለማችን ሀገራት የእርስ በርስ ግብይቶቻቸውን በየራሳቸው መገበያያ ገንዘቦች በማድረግ ላይ መሆናቸው የአሜሪካ ዶላር በዓለም ንግድ ላይ ያለውን ድርሻ እያዳከመው እንደሚሄድም ተገልጿል፡፡
ይሁንና አሁንም የዓለም ግማሹ ሀብት በአሜሪካ ዶላር መልኩ መኖሩ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በዶላር እየተሳለጠ መሆኑ እና የዶላርን ያህል ተቀባይነት ያለው ሌላ መገበያያ ገንዘብ አለመኖሩ የዶላር የበላይነቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
ይሁንና በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ያልተማከለ ንግድ ስርዓት እንዲኖር መፈለግ እና በአሜሪካ ዶላር ላይ እምነት ማጣት ሀገራት እና የንግድ ተቋማት ተጨማሪ መገበያያ ዘዴ በመፈለግ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡