በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች የዶላርን የበላይነት ሊቀንሱ እንደሚችሉ አይ ኤም ኤፍ አሳሰበ
ተቋሙ፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የኢኮኖሚ ውድቀት አይከሰትም ብሏል
ቭላድሚር ፑቲን ዶላር “የሚታመን መገበያያ አይደለም” ብለው ነበር
በሩሲያ ላይ የተጣሉ የገንዘብ ማዕቀቦች የዶላርን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሊቀንሱት እንደሚችሉ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) አስታወቀ።
የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጊታ ጎፒናዝ አሁን ላይ አሜሪካን ጨምሮ የተለያያ ወገኖች በሞስኮ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች የዓለምን የገንዘብ ሥርዓት የተበታተነ ሊያርገው እንደሚችል ገልጸዋል።
ሩሲያ “ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ” በሚል በዩክሬን የጀመረችው ዘመቻ በርካታ ማዕቀቦችን አስከትሎባታል።
ይህንን ተከትሎም ሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች የዶላርን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዳይሻሙ ስጋት የገባቸው የአይ ኤም ኤፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ ዶላር አሁንም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ሊቀጥል ቢችልም ስጋቶች እንዳሉ ግን ተናግረዋል።
በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለው ጦርነት የገንዘብ ዝውውሩን በዲጂታል መንገድ እንዲሆን አድርጎታል ነው የተባለው።
ከዶላር ውጭ ያሉትን የመገበየያ ገንዘቦችን በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ መጠቀም በየማዕከላዊ ባንኮች የሚኖረውን ተቀማጭ ገንዘብ የተለያየ እንደሚያደርው ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። እንደሚቀጥል ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሯ መጠነኛ መንገጫገጭ እንደሚኖርም ተናግረዋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለው ጦርነት የኢኮኖሚ ዕድገትን ቢያቀዛቅዘውም የኢኮኖሚ ውድቀትን እንደማያስከትል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጊታ ጎፒናዝ ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ከዚህ በኋላ ጋዝ የምትሸጠው በራሷ የመገበያያ ገንዘብ “ሩብል” እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል። የዚህ ውሳኔ ተግባራዊነትም በፍጥነት እንዲከናወን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) ከሳምንት በፊት ባሰራጨው ዘገባ ሞስኮ ከዚህ በኋላ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር “በዩሮም ሆነ በዶላር የመገበያየት ስሜት የላትም” ብሏል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጊታ ጎፒናዝ የዶላር ተጽዕኞ ፈጣሪነት ሊሸረሸር እንደሚችል የገለጹት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዶላር የሚታመን የመገበያያ ገንዘብ እንዳልሆነ ከተናገሩ ከሳምንት በኋላ ነው።